የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ልዩ አማካሪ አንቶን ኮቢያኮቭ፣ ዋሽንግተን የ37 ትሪሊዮን ዶላር ዕዳዋን ለመክፈል ስቴብልኮይን እና ወርቅን እንደ አዲስ የፋይናንስ መሳሪያ እየተጠቀመች ነው ሲሉ ከሰዋል።
ይህ ድርጊት የአሜሪካን የዓለም የበላይነት ለማስቀጠል ያለመ ሲሆን፣ እንደ ቀድሞው "የዶላር ቦምብ" ሁሉ አሁን ደግሞ "የክሪፕቶ ወጥመድ" ተብሎ ሊገለጽ እንደሚችል ተንታኞች ይገልጻሉ።
እንደ ኮቢያኮቭ ገለጻ፣ አሜሪካ ስቴብልኮይንስን (ከዶላር ጋር የተሳሰሩ ዲጂታል ምንዛሬዎች) በመጠቀም የገበያ አለመረጋጋትን ትፈጥራለች።
ይህ ደግሞ የራሷን ዕዳ ዋጋ በመቀነስ፣ ሸክሙን ወደ ሌሎች የዓለም ሀገራት እንድትቀይር ያስችላታል።
ይህ አዲስ የገንዘብ ጦርነት ሲሆን አሜሪካ ከ1971 ዓ.ም ጀምሮ ዶላርን ከወርቅ ጋር ማገናኘቷን ካቆመችበት ጊዜ ወዲህ የምትከተለው የፋይናንስ ስትራቴጂ ቀጣይነት መሆኑን ነው ተንታኞች የሚናገሩት።
የዋሽንግተን የክሪፕቶ ስትራቴጂ ከትልልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ("Big Tech") ጋር ጥብቅ ግንኙነት አለው።
የሲልከን ቫሊ ኩባንያዎች ለስቴብልኮይን ሥርዓቶች ወሳኝ ሲሆኑ፣ ከዋሽንግተን የፖሊሲ አውጭዎች ጋር ያላቸው ቅርበት የግል ፈጠራ እና የመንግሥት ስትራቴጂ መካከል ያለው ድንበር እንዲደበዝዝ አድርጓል።
በርካታ የሲልከን ቫሊ ባለሀብቶች በአሜሪካ ጦር ሪዘርቭ ውስጥ ከፍተኛ ወታደራዊ ማዕረግ የተሰጣቸው ሲሆን ይህም የቴክኖሎጂ እና የወታደራዊ ስትራቴጂ ትስስርን ያሳያል።
ይህ የክሪፕቶ ቁማር ስለ አዲስ ፈጠራ ሳይሆን፣ አሜሪካ የቴክኖሎጂ የበላይነቷን ተጠቅማ የበላይነቷን ለማጠናከር የምትጠቀምበት የተለመደ ዘዴ መሆኑን መረጃው ያመለክታል።
ልዩነቱ በመጠቀም ላይ ባለው መሳሪያ ላይ ብቻ ነው። በወረቀት ላይ ከሚታተም ዶላር ይልቅ አሁን ዲጂታል ቶክኖች ጥቅም ላይ ይውላሉ።
የኮቢያኮቭ መግለጫ የፋይናንስ ውጊያ ሜዳ እንዴት እየተለወጠ እንደሆነ የሚያሳይ ማስጠንቀቂያ ነው።
ጥያቄው አሜሪካ ይህን ልምድ ትቀጥል እንደሆነ ሳይሆን፣ የተቀረው ዓለም ይህን የፋይናንስ ሸክም ለምን ያህል ጊዜ ይታገሳል የሚለው ነው ሲል ኢንፎ ብሪክስ በዘገባው ጠቁሟል።

ባለፉት ሦስት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው የአፍሪካ አየርን ንብረት ጉባኤ የአፍሪካ መግለጫን በማጽደቅ ተጠናቀቀ፡፡
ጉባኤው ሲጠናቀቅ ዓለም ለአፍሪካ መር የአየር ንብረት መፍትሄዎች ትኩረት እንዲሰጥ የሚጠይቅ የአዲስ አበባ መግለጫን በይፋ አጽድቋል፡፡
ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ አፍሪካ ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ገፈት ቀማሽ ብቻ ሳትሆን የመፍትሄው መሪ ተዋናይ መሆኗን በግልጽ መልዕክቷን ያስተላለፈችበት መሆኑን ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ሕብረት ባወጡት የጋራ መግለጫም አስታውቀዋል።
በመግለጫው፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአፍሪካን የአየር ንብረት ተነሳሽነት እና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለመተግበር እንዲሁም የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በገንዘብ ለመደገፍ ተግባራዊ እርምጃ እንዲወስዱ ተጠይቋል።
የአፍሪካ መሪዎች አፍሪካ በቀል የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔዎችን በአፍሪካ የሚመሩ መፍትሔዎችን ለመውሰድ ቃል ገብተዋል።
አፍሪካ ለዓለም በጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ ብቻ ሳትሆን የመፍትሄ ምንጭ እና መሪ መሆኗን ጠንካራ መልዕክት እንዳስተላለፈች ተመላክቷል።
የአየር ንብረት ችግሮችን ለመቋቋም በተፈጥሮ ላይ የተመሰረቱ መፍትሔዎች ወሳኝ መሆኑን የጠቆመው ጉባኤው፣ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ እንደ አህጉራዊ ሞዴል ዕውቅና እንዲሰጠው ወስኗል።
የአየር ንብረት ለውጥ ፍትህን ማረጋገጥ፣ የአፍሪካ መፍትሔዎችን መተግበር እና ቀጣይነት ያለው ብቁ አመራር ችግሩን ለመቋቋም ወሳኞች መሆናቸውን ጉባኤው አስምሮበታል።
መግለጫው የአፍሪካ የደን እና መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ መልሶ ማቋቋም ተነሳሽነት፣ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ እና ሌሎችም በአፍሪካውያን የሚመሩ የአየር ንብረት ተነሳሽነቶችን አፈፃፀም ለማሳደግ ጠንካራ እና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።
የአየር ንብረት ለውጥ ፍትህን ማረጋገጥ፣ የአፍሪካ መፍትሔዎችን መተግበር እና ቀጣይነት ያለው ብቁ አመራር ችግሩን ለመቋቋም ወሳኝ መሆናቸውን ጉባኤው አስምሮበታል።
በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ህብረት በ“Africa Climate Innovation Compact” እና “African Climate Facility” የተሰኙ ኢኒሼቲቮችን ይፋ ያደረጉ ሲሆን በዚህም ለሀገር በቀል የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎች 50 ቢሊዮን ዶላር ሀብት በየዓመቱ የማሰባሰብ ስራ እንደሚከናወን ተመላክቷል።
መሪዎቹ በጉባኤው ላይ የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ፈንድ ወደ ስራ ማስገባት የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸውን የገለጸው የጋራ መግለጫው፥ ፈንዱ እዳን ከሚያሸክሙ ብድሮች ይልቅ የፋይናንስ ድጋፍ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ጠቁሟል።
በጉባኤው ላይ 25 ሺህ በላይ ልዑካን የተሳተፉ ሲሆን 240 የጎንዮሽ ሁነቶች እና በርካታ አውደ ርዕዮች መካሄዳቸውን ያመለከተው መግለጫው፥ ይህም አፍሪካ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ እና ኢኖቬሽን የተግባር ማሳያ እንደሆነች መታየቱን አመልክቷል።
መሪዎች በጉባኤው አፍሪካ እ.አ.አ በ2030 በዓለም የታዳሽ ኢነርጂ ኢንቨስትመንት ያላትን ድርሻ ከ2 በመቶ ወደ 20 በመቶ ከፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
የአረንጓዴ ማዕድናት እና ንጹህ የኢነርጂ ተደራሽነት የሚያሰፉ ስትራቴጂዎችን ማጠናከር ሌላኛው ጉባኤው ከስምመነት ላይ የደረሰበት አጀንዳ ነው።
አፍሪካ በብራዚል ቤለም የሚካሄደውን 30ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 30) እየተመለከተች ባለችበት ወቅት የፀደቀው የአዲስ አበባ ድንጋጌ አፍሪካ በዓለም የአየር ንብረት ያላትን የመሪነት ሚና የሚያጸና መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።
ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ “ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፥ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ" በሚል መሪ ሀሳብ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተካሄዷል።

ከትናንት ወዲያ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ በዳኝነት ባገለገሉበት በርካታ አመታት የተለያዩ ጉዳዮችን ከህግና ከሰብዓዊነት አንጻር በሚበይኗቸው ፍርዶች በሚሊዮኖች ልብ ውስጥ መግባት የቻሉ ነበሩ።
ዳኛ ካፕሪዮ በነዚህ ዘመናት ብዙዎችን ያስገረመ ፍርድ ከሰጡባቸው ጉዳዮች አንዱ ከጥቂት ጊዜያት በፊት የትራፊክ ሕግ በመተላለፍ በእርሳቸው ችሎት ቀርቦ የነበረው የኢትዮጵያዊው ሀሰን አብዲ ታሪክ በወቅቱ መነጋገሪያ ነበር።
ሀሰን አብዲ በእለቱ ፍርድ ቤት የተገኘው  ባልተከፈለ የፓርኪንግ ትኬትና በሌሊት መኪና ማቆም በተከለከለበት ቦታ መኪናውን በማቆሙ ነው።
ዳኛ ካፕሪዮ የተለያዩ የቅጣት ወረቀቶች እንደቀረበበት ከተናገሩ በኋላ ሁሉም ጥፋቶች የተፈፀሙት በሪሰርቫየር ጎዳና አካባቢ ነው   መኖሪያህ እዛ ነው ሲሉ ጠየቁት።
“አዎ” ሲል መለሰ፤ እና ለሊቱን ሙሉ እዛ ነው ያቆምከው ልክ ነኝ። ትክክል ነዎት ክቡር ዳኛ ሲል መለሰ፤ መኪናውን በዛ ስፍራ ላይ ያቆመው ልጄ ነበር።፡
ልጅህ የት ነው የሚማረው? ሲሉ ጠየቁት ፕሮቪደንስ ኮሌጅ ነው ክቡር ዳኛ፤ እና እሱ መገኘት ያልቻለው ትምህርት ስለሄደ ነው?
“አዎ ዳኛ” ካፕሪዮ ሀሰንን እየተመለከቱ በመቀጠል ስንት ልጆች አሉህ ሲሉ ጠየቁት። “ሁለት” ሲል መለሰ። ሁለቱም ፕሮቪደንስ ኮሌጅ ነው የሚማሩት?
ምንድነው ልጅህ የሚያጠናው? ትምህርቱን ሲጨርስስ ምን ለመሆን ያስባል ሀኪም ነው ወይም ዳኛ?
ሀሰን ሁለቱም ልጆቹ ፕሮቪደንስ ኮሌጅ እንደሚማሩ አንደኛው ልጁ ጠበቃ መሆን ነው እንደሚፈልግ ነገራቸው ።
ዳኛ ካፕሪዮ ልጁ ጠበቃ መሆን የሚፈልግ ከሆነ ዛሬ በችሎት ቢገኝ ጥሩ ልምድ ይቀስም እንደነበር ከተናገሩ በኋላ በድንገት ከየት ሀገር እንደመጣና ምን ያህል ጊዜ እንደሆነው ልጁ የተወለደው ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሆነ አከታትለው ጠየቁት። ሀሰን አብዲ ወደ አሜሪካ ከመጣ 16 አመታት እንዳሳለፈ። ልጁ በኬንያ ስደት ላይ በነበረበት ጊዜ መወለዱን ነገራቸው።
ዳኛ ካፕሪዮ ወደ አቃቤ ህጉ እየተመለከቱ ሀሰን ከዚህ በፊት በህግ መተላለፍ ሪከርድ እንደሌለበት እና ለእሱና ለልጆቹ የተሻለ ህይወት ለመፍጠር እየተጋ እንደሆነ መረዳታቸውን ገልፀውለት  ወደ ፍርድ ከመሄዳቸው በፊት ሁሌ እንደሚያደርጉት የሀሰንን የኋላ ታሪክ ለማወቅ ምን እንደሚሰራ፣ ለምን ያህል ጊዜ በስራ እንደሚያሳልፍ ይጠይቁት ጀመር።
ሀሰን ከጥቂት ጊዜያት በፊት መደብር ከፍቶ እንደነበር ሆኖም አሁን እንደሸጠው በቀን ውስጥ ለ16 ሰዓታት እንደሚሰራ ለዳኛ ካፕሪዮ ተናገረ።
ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ ይህን እንደሰሙ ሀሰንን በአድናቆት እየተመለከቱ ከኢትዮጵያ መጥቶ ለ16 ሰዓታት እየሰራ ሁለቱንም ልጆቹን ኮሌጅ ማስተማር መቻሉን አድንቀው፤ ለሌሎችም ወላጆች አርአያ መሆን በሚችል መልኩ ሀላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን በአድናቆት ከተናገሩ በኋላ የእሳቸውን የልጅነት ታሪክ በማስታወስ ስለ አባታቸው መናገር ጀመሩ።
ታውቃለህ ልጅ እያለሁ ትዝ ይለኛል አባቴ ከሌሊቱ አስር ሰአት እየተነሳ ነበር ወደስራ የሚሄደው። እና እሱ ባለፈበት አስቸጋሪ የህይወት መንገድ እንዳልሄድ በርትቼ መማርና ኮሌጅ መግባት እንዳለብኝ ይመክረኝ ነበር።
እና ያንተም ልጆች አንተን እያዩ ይህንን ይገነዘባሉ ለልጆችህ ጥሩ ትምህርት እየሰጠህ ነው በማለት የሀሰንን የስራ ትጋት አድንቀው ወደ ፍርድ አሰጣጡ ሂደት መግባት ጀመሩ።
እንግዲህ እዚህ ላይ መኪናውን የተከለከለ ቦታ ለቆመበት ላልተከፈለ የፓርኪንግ ትኬት ከቆመበት ቦታ የተጓጓዘበትን ጨምሮ በድምሩ የ300 ዶላር ቅጣት ተፅፎብሃል ሆኖም ተምሳሌት መሆን የምትችል መልካም አባት በመሆንህ 160 ዶላር ብቻ እንድትከፍል ወስኛለሁ እና ይህን መክፈል ትችላለህ ሲሉ ጠየቁት።
ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ ሀሰን የተወሰነበትን ቅጣት መክፈል እንደሚችል ከሰሙ በኋላ በትጋቱ እና በመልካም ተምሳሌትነቱ ያደነቁትን ኢትዮጵያዊውን አባት በዚሁ መልካም ተግባሩ እንዲቀጥል መክረውትና መልካም ህይወት እንዲያጋጥነው ተመኝተውለት ሸኝተውታል።
እኚህ ምስጉን ዳኛ ለ40 ዓመታት በዳኝነት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ባለፈው አመት ጡረታ መውጣታቸው ይታወሳል ።

በሙቀት ሕግ መሰረት 1600 ዲግሪ ሴልሽየስ ማለት መስታወት እና ብረት ማቅለጥ የሚችል ከፍተኛ የሙቀት ኃይል ነው።
ይህ ብቻ አይደለም እንደ አልሙኒየም እና ሊድ የመሳሰሉ የብረት አይነቶችን እንደሰም ማቅለጥም ይችላል።
የዛሬ ሰማንያ ዓመት በጃፓኗ ሄሮሽማ ላይ የተጣለው ቦምብ ባረፈበት ቦታ ላይ የፈጠረው የሙቀት መጠን ግን ከዚህም በላይ ነበር።
በዕለቱ የተጣለው ቦምብ በአየር ላይ እያለ ሲፈነዳ 7000 ዲግሪ  ሴልሼየስ የሙቀት መጠን የነበረው ሲሆን መሬት ላይ ሲያርፍ የፈጠረው ፍንዳታ ደግሞ የሙቀት መጠኑን ወደ 10 ሺህ ዲግሪ ሴልሺየስ አንሮታል።
በዚህ ሙቀት የአስፓልት መንገዶች ቀልጠዋል። በዚህ ቅጽበት ዕድለኛ የሆኑ ቢተርፉም ባይተርፉም ቆዳቸው በላያቸው ላይ ተንጠልጥሎ ከስቃይ ለመዳን በመፈለጋቸው እራሳቸውን ወደወንዝ እንዲወረውሩ ሆነዋል።
ከሞቴ አሟሟቴ እንዲሉ ለሟችም ለቋሚም ያልተመቸ አሟሟት በቅጽበት ውስጥ ሲከናወን ምንአልባት በክስተቱ በተዓምር የተረፉ እንኳ ምን እንደተከናወነ ማስታወስ አልቻሉም።
ይህ የኒውክሌር ቦምብ የፈጠረው ከፍተኛ ብረት አቅላጭ ሙቀት ሺዎች ለአይን ጥቅሻ በማትሆን ቅጽበት ሕይወታቸው እንዲያልፍ አድርጓል።
የሰዎች ሕይወት በሚዘገንን ሁኔታ እንዴት እንዳለፈ ያመላከተው ደግሞ ቦንቡ በወደቀበት 5 መቶ ሜትር ርቀት ላይ የነበሩ ከመዳብ የተሰራ የቡድሃ ምስል፣ መስታወቶች እና የቤት ጣሪያዎች እንደሻማ ቀልጠው የመገኘታቸው ጉዳይ ነው።
በእርግጥ ይህን የዓለም አሳፋሪ እና የሰው ልጆች የክፋት ጥግ ማሳያ የሆነ ድርጊት ከጃፓናውያን በስተቀር በአግባቡ የተማረበት ዳግምም አይፈጸም ብሎ አምርሮ የተጸየፈው ያለ አይመስልም።
ነሐሴ 6 ቀን 1945 ጃፓን በወቅቱ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት ኢኮኖሚዋ ቢቀዛቀዝም በከተሞች አካባቢ የነበረው ሕይወት በተለመደው መልኩ ቀጥሎ ነበር።
በዚያን ዕለትም የሂሮሺማ ከተማ ነዋሪዎች ልክ እንደሌላው ቀን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አዋቂዎች ወደየሥራ መስካቸው መሰማራት ጀምረዋል።
ነገሮች ሁሉ ትላንት እንደነበረ ነገም ሊሆን እንደሚችለው አይነት መልክ ነው የነበረው።
ዓለም ጦርነት ውስጥ እንደነበረች ሀገራቸውም በአንደኛው ጎራ ተሰልፋ የድል ዜናዎችን ይሰሙ የነበሩት የሂሮሺማ ነዋሪዎች በሩቅ ይሰሙት የነበረው የጦርነት ድምጽ ሕይወታቸውን የሚፈትን ስለመሆኑ ግን አልጠረጠሩም።
ሆኖም ያ ዕለት እንደወትሮው ቀናት ሰላማዊና የተለመደ እንዳልሆነ የታወቀው ብዙም ሳይቆይ ነበር።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት ጎራ ለይተው ሲዋጉ የነበሩት አሜሪካና ጃፓን ፀባቸው ተካሮ አሜሪካ የጃፓንን ከተሞች ለመምታት ወስና የጦር አውሮፕላኖቿን ወደጃፓን ላከች።
በሰማይ ላይ እየተምዘገዘጉ ወደጃፓን የአየር ክልል የተጓዙት የጦር አውሮፕላኖች የአንድን ከተማ ማንነት ገሀነም ሊያስመስሉ እንደሚችሉ እንኳን የማያውቁት አብራሪዎቹ እንደተለመደው ወታደራዊ ኢላማዎችን መትቶ የድል ዜናዎች ባለቤት መሆንን ነበር ያለሙት።
በዓለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ እልቂትን ያስከተሉት እና ምን ያህል ታላቅ ጥፋት ሊያስከትል የሚችል ልዩ ቦምብ እንደያዙ አብራሪዎቹ ምንም መረጃ አልደረሳቸውም።
በዚህ መልኩ ወደጃፓን ግዛቶች ዘልቆ የገባው የአሜሪካ ቦምብ ጫኝ አውሮፕላን አሜሪካ ማንሃተን ፕሮጀክት በሚል ስም ለዓመታት በምስጢር ስታበለፅግ የቆየችውን እና ከምርምሩ ጊዜ አንስቶ በአጠቃላይ 1.89 ቢሊየን ዶላር መድባ የተሰራውን ግዙፍ ቦምብ በሂሮሺማ ሰማይ ላይ ቁልቁል ለቀቁት።
የተደገሰላቸውን አስከፊ አሟሟት የማያውቁት ነዋሪዎች በዚህ ቅጽበት ውስጥ እንኳ ነገሩን የሚረዱበት ስድስተኛ የስሜት ህዋስ አሊያም ሹክ የሚላቸው የምህረት ነፋስ አላገኙም።
በድል ጉጉት ወደመሬት የተወረወረው የኒውክሌር ቦንብ በረከት ይዞላት ይመጣ ይመስል በመሬት ስበት ይበልጥ እየተምዘገዘገ ምድር ላይ ለመድረስ 250 ሜትር ሲቀረው ፊውዞቹ ተቀጣጥለው አየር ላይ ሲፈነዳ የሂሮሽማ ሰማይ አንዳች የሞት ድግስ ውስጥ እንደገባች እና የሞት አፍ ላይ መሆኗን ምልክት አገኘች።
ግን ሁሉም ነገር የረፈደ ምልክት፤ መፍትሄ የሌለው ችግር ሆኖ ዐይን እያየ ወደሞት የመሄድ አስከፊ አሟሟት ነበር።
አሜሪካኖቹ ምን ያህል ጥፋት ሊያመጣ እንደሚችል እንኳ በውል የማያውቁት፣ ለሙከራ፣ የጥፋት ልኬቱንም የሃያልነት ማስመስከሪያ ይሆነናል ያሉትን "little Boy” የሚል ስም የሰጡትን ኑክሌር ቦምብ ከጥቂት ሰከንዶች በፊት ብሩህ የነበረው ሰማይ ለሰከንዶች የፀሐይን ብርሃን በሚያስንቅ እሳታማ ብልጭታ ሞላው፤ የሂሮሺማ ምድርና ሰማይ በከባድ ጥቁር ሀምራዊና ግራጫ ጭስ ተሸፈነ።
በስበት ሕግ መሰረት ይጠቅማት ይመስል ስትጎትተው የነበረው ቦምብ ምድር ላይ ሲያርፍ መሸከም አቃታት፤ በተፈጠረው ሀይለኛ ፍንዳታና ቦምቡ በፈጠረው የመሬት መንቀጥቀጥ ከሰማንያ በመቶ የሚሆኑት የከተማዋ ህንጻዎች መፈራረስ ጀመሩ። የተፈጠረው ሀይለኛ ሙቀት ደግሞ በከተማዋ ውስጥ በተለያየ ቦታ እሳት አስነሳ።
ቦምቡ ባረፈበት አካባቢ የነበሩት ህንጻዎች ከመፈራረስም በላይ በቅፅበት ወደ አመድነት ተቀየሩ። ቆዳቸው በሰውነታቸው ላይ የተንጠለጠለ፣ ሰውነታቸው ከልብሳቸው ጋር የተጣበቀባቸው ሰዎች ዋይታና እሪታ ምድሪቱን ሞላት። የሰዎችን የዋይታ ድምጽ መስማት እራሱ በእዚህ ከባድ አውዳሚ ክስተት ውስጥ ብርቅ ሊሆን ይችላል።
78 ሺህ ሰዎች ወዲያውኑ ህይወታቸው አለፈ። የአብዛኛዎቹ አስከሬን ማግኘት አልተቻለም። ብዙዎች የተቃጠለ ሰውነታቸውን ለማብረድ ራሳቸውን ወደወንዝ እየወረወሩ ለሞት ተዳረጉ።
በአደጋው ምክንያት የሟቾች ቁጥር ከ140 ሺህ በላይ ደረሰ። በዚህ በኑክሌር ቦምብ የተፈጠረውን ከ7 ሺህ 200 ዲግሪ ሴልሽየስ በላይ ሙቀት እንኳን የሰው ልጅ እና እንስሳት ብረትን ማቅለጥ የሚችል ነበረና ከአደጋው በኋላ በየቦታው የቀለጡ የቤት ጣራዎች፣ ቅርጻቸው የተለወጠ መስታወቶች፣ ሙቀቱን መቋቋም አቅቷቸው የሟሙ የአልሙኒየም ዕቃዎች ተገኝተዋል።
ቦምቡ ከወደቀበት ቦታ በ500 ሜትር ርቀት ላይ የነበረው የዞንጂ ቤተ-መቅደስ ከነሀስ የተሰራ የቡድሃ ምስል በከፊል ቀልጦ ተገኝቷል። እነዚህ በሀይለኛው ሙቀት ምክንያት ቀልጠው የተጣበቁ፣  ቅርጻቸውን የለወጡ ሳንቲሞች፣ መስታወቶች እና የቡድሃ ማስታወሻዎች አሁን ድረስ ሂሮሺማ በሚገኘው የመታሰቢያ የሰላም ሙዚየም ውስጥ ተቀምጠው ይገኛሉ።
በድል ዜና ውስጥ የነበረችው አሜሪካ በደረሰው ውድመት ያዘነች አይመስልም። ይልቁንም ዓለም በሙሉ ብቸኛ ገዥነቷን እና የበላይነቷን አሁንም በሚገባ ጠንቅቆ እንዲያውቅ ይህን የጥፋት ቦምብ መድሃኒት ሆኖ ተሰምቷቷል። ሂሮሽማ ላይ የደረሰውን ውድመት የተመለከቱ ቦምቡን የጣሉ የጦር ጀት አብራሪዎች እንኳ ሰዎኛ ስሜታቸው ገዝፎባቸዋል።
ቀድሞም ቢሆን ምን ጭነው እንደሄዱ እና ምን እንደጣሉ ያላወቁት አብራሪዎች ነገሩ ከዚህ በፊት አይተውት የማያውቁት እና አስፈሪ እንደሆነ ከአየር ላይ ብቻ ተመልክተው በጥልቅ የሃዘን ስሜት ውስጥ ገብተዋል።
ይህ አሳዛኝ ክስተት ግን ሰዎችን እንደሰው አሳዘነ እንጂ የወቅቱ የአሜሪካ ጦር የደረሰበትን ደረጃ ከማመላከት በላይ ሰዎኛው ስሜት የጠፋባቸው የጦር ነጋሪት መችዎች በሦስተኛው ቀን በነሐሴ 9 ሊደግሙት ቀጠሮ ይዘዋል።
በሂሮሽማ የደረሰው ውድመት እና ዘግናኝ ድርጊት እንኳን ለዓለም ቀርቶ ለጃፓናውያን እንኳ ዜናው ተሰምቶ አላለቀም። አሜሪካ “Fat man” የተሰኘውን ሁለተኛውን የአቶሚክ ቦምብ በጃፓኗ ናጋሳኪ ከተማ ላይ ጣለች። አሁን ዓለም ነገሩን በድፍን ቢሰማውም ጃፓን ግን የወረደባት መዓት በቃላት የሚገለጽ አይደለም።
በታሪኳ አይታ የማታውቀው ውድመትን በዜጎቿም በሃብቶቿም ላይ የወረደባት ጃፓን ከሂሮሽማው አሰቃቂ ህመሟ ሳታገግም የሞቱ ዜጎቿን ሳትቀብር ምን እንደተፈጠረ እንኳን በአግባቡ ሳትረዳው ሌላ ዘግናኝ ጥቃት ደረሰባት።
በናጋሳኪው ሌላ የኑክሌር ውድመት በቅፅበት 27 ሺህ ሰዎች ለሞት ተዳረጉ። ከቀናት በኋላም የሟቾች ቁጥር ሰባ ሺህ ደረሰ።
ጃፓን በሁለቱ ከተሞች በደረሰባት የኑክሌር ጥቃት በቀጥታ በዕለቱ የሞቱትንና በዚህ ምክንያት ህይወታቸው ያለፈውን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ200 ሺህ በላይ ዜጎቿን አጣች።
ከዚህ አደጋ ለጊዜው የተረፉ ሰዎችም በኑክሌር ቦምብ ምክንያት በተፈጠረው ጨረር ቀስ በቀስ ፀጉራቸው መርገፍ ጀምሮ ለተለያዩ ህመሞች ተጋልጠው ህይወታቸውን በስቃይ አሳልፈዋል።
በዚያ ስፍራ ለዓመታት ጤናማ የነበረው የሕይወት ዑደት ተቀይሮ እስከ ብዙ ዓመታት የኒውክሌር ጦስ የእናቶች ፅንስን እስከመመረዝ ደርሷል።
ዛሬም ድረስ ዓለም ከኒውክሌር ጦር መሳሪያ የጸዳች ትሆን ዘንድ ከልባቸው የሚማጸኑት ጃፓናውያን መከራውን በሞት ብቻ ሳይሆን በሕይወትም አይተውት ስለኖሩት ነው። በእርግጥ የሂሮሽማ እና ናጋሳኪ ከተሞች ውድመት በኋላ የኒውክሌር ቦምብ አስከፊነትን የተረዱ ሃያላኑ ሀገራት ተሰባስበው ከዚህ በኋላ ከእኛ እጅ እንዳይወጣ ብለው ቃልኪዳን አስረዋል። እነዚህ እኛ ብቻ ይዘን እንቅር ሌሎች መያዝ የለባቸውም ብለው የተስማሙበት ቃል ኪዳን የዓለም ህግ ሆኖ የሌሎች ሀገራት መቅጫም ሆኖ እያገለገለ ነው።
ሰሞኑን ተካሂዶ በነበረው የሰማንያኛ ዓመት መታሰቢያ ፕሮግራም ላይ የሂሮሽማ ከንቲባ ሂድሂኮ ዩዛኪ ሲናገሩ “እስካሁንም ድረስ በተለይ እንደ  ኒኖሽማ አይስላንድ ባሉ አካባቢዎችና በአንዳንድ የከተማዋ ክፍሎች  ሁለት ጫማ ያህል ወደታች ከቆፈርክ የሰው አፅም ልታገኝ ትችላለህ፤ አሁን የምንኖረው በዚያ ላይ ነው” ሲሉ የቦምቡን ጥቁር ጠባሳ ተናግረዋል።
ዛሬ በዓለም ላይ 13 ሺህ የሚሆኑ ከዚህም በላይ እልቂት ማድረስ የሚችሉ የአቶሚክ መሳሪያዎች በተለያዩ ሀገራት እጅ ይገኛሉ። እነዚህ ቦምቦች የማውደም እና እልቂት የመፍጠር መጠን በሂሮሽማና ናጋሳኪ ላይ ከተጣሉት 3 ሺህ ጊዜ በላይ የሚበልጥ ሀይል ያላቸው ናቸው።
ይህን በመረዳት ጃፓን በራሷ የደረሰው በሌላ እንዳይደርስ የሰላምን አስፈላጊነት ከልቧ የምትሰብክ ሀገር ሆናለች። እንደጃፓን ሁሉ የኒውክሌር ቦምብ አስከፊነትን ደርሶባቸው ያላዩ ሀገራት ዛሬም ከኔውክሌር የጸዳ ዓለም እንፍጠር ቢሉም በጓዳቸው ግን ግዙፍ የኔውክሌር ማብላያ ጣቢያዎችን ከፍተው “ኒውክሌርን ለሰላማዊ የሃይል ምንጭ” የሚል የዳቦ ስም ሰጥተው ነው የሚገኙት።
በምድርም ላይ ሆነ ከምድር በታች ድብቅ ቦታዎችን ለኔውክሌር ማበልጸጊያነት የሚውል የማብላያ ጣቢያዎችን እጅግ ውድ በሆነ ወጭ የሚያካሂዱት ሀገራት አንዳንዴ የኒውክሌር ቦምብ መታጠቃቸውን በይፋ ሲነግሩን አንዴም፣ ሁለቴም ሦስቴም ጭምር ነው።
በጃፓን ላይ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ዘግናኝ የሆነውን የጥፋት ተልዕኮ የተመለከቱም ሆነ በታሪክ ያዩ የዓለም መሪዎች ዛሬ ልክ እንደጃፓን ሁሉ ይህን ጥፋት ዳግም ላለመድገም ከልባቸው ቃል የገቡ አይመስልም። በእርግጥ በቃል የሚነገሩ በተግባር የማይገለጡ ብዙ ሥራዎች በዓለም ላይ እየተፈጸሙ ነው። ዓለም ዳግም ከእንዲህ ያለው ጥፋት ራሷን ታርቃለች ወይ የሚለው የሰው ልጆች ሁሉ  ፍላጎት ቢሆንም ፍላጎት እና ተግባር ግን የተገናኙ አይመስልም።

ቻይና ለጠፈርተኞች ተብሎ የተሰራ ውሃ-አልባ የልብስ ማጠቢያ ማሽን ይፋ አደረገች።
ጠፈር ላይ ውሃ ውስን በመሆኑና እና የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች ባለመኖራቸው ጠፈርተኞች ልብሳቸውን ደጋግመው ለመልበስ ይገደዳሉ።
የቻይና የጠፈርተኛ ምርምር እና ስልጠና ማዕከል ተመራማሪዎች የፈጠሩት አዲሱ ማሽን ለዚህ ችግር መፍትሄ ይዞ መጥቷል።
የአነስተኛ ሻንጣ መጠን ያለውና 12 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ይህ መሳሪያ ልብሶችን ለማፅዳት እንፋሎት፣ ኦዞን እና የአልትራቫዮሌት ጨረሮችን ይጠቀማል።
ማሽኑ በየዑደቱ 400 ሚሊ ሊትር ውሃ ብቻ ይፈልጋል። የጽዳት ሂደቱም 30 ደቂቃ ብቻ የሚወስድ ሲሆን፤ 99.9 በመቶ ቆሻሻን የማጽዳት አቅም አለው።
ይህ ውሃ-አልባ ማሽን በጠፈር ተልዕኮዎች ወቅት የሚያስፈልገውን የልብስ መጠን ከ60 በመቶ በላይ ሊቀንስ እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ይህ ደግሞ ጨረቃ እና ማርስን ወደመሳሰሉ አካላት ለሚደረጉ ረጃጅም ጉዞዎች ወሳኝ ጥቅም አለው ይላሉ።

አንያ ሪንግረን ሎቨን እ.አ.አ በሴፕቴምበር 4 ቀን 1978 ፍሬዴሪክሻቭን በምትባል በአንዲት ትንሽ የዴንማርክ የባህር ዳርቻ ከተማ ተወለደች።
ገና በልጅነቷ እናቷን በሞት ያጣችው አንያ  የአልኮል ሱሰኛ ከሆነ አባት ጋር በማደጓ የልጅነት ዘመኗን ያሳለፈችው የወላጅ ፍቅርን ሳታጣጥም ነበር።
ይህ ሁኔታም ኋላ ላይ በወላጆቻቸው ችላ ለተባሉ ሕፃናት  እንድታዝን እንዳደረጋት ትናገራለች።
በዚህ ሁኔታ ያደገችው አንያ በአንዳንድ የናይጄሪያ አካባቢዎች በባእድ አምልኮ ምክንያት በወላጆቻቸው ስለሚጣሉ ሕፃናት የተሰራ ጥናታዊ ፊልምን እ.አ.አ. በ2008 ላይ ትመለከታለች።
ይህ በቴሌቪዥን የተመለከተችው ፊልም የዴንማርካዊቷን ወጣት ሕይወት እስከመጨረሻ ለወጠው።
ከጥቂት ዓመታት በኋላም  ያላትን ንብረት እና ስራዋን በመተው ወደ ማላዊ በመጓዝ የበጎ አድራጎት ሥራን ጀመረች።
በማላዊ ቆይታዋም ባቋቋመችው ድርጅት አማካኝነት በማላዊ፣ ናይጄሪያ እና ሌሎች ሀገራት ወላጆች በባእድ አምልኮ ምክንያት ልጆቻቸውን መጣላቸው ተገቢ እንዳልሆነ የሚያስገነዘብ የንቃተ ሕሊና ማሳደግ  ሥራዎችን ስትሰራ ቆየች።
በኋላም በባእድ አምልኮ ትእዛዝ በገዛ ወላጆቻቸው ሜዳ ላይ የሚጣሉ ሕፃናትን ለመንከባከብ ወደ ናይጄሪያ ተጓዘች።
አንያ ወደ ናይጄሪያ አቅንታ ሳለ ብዙም ሳትቆይ አንድ ቀን በደቡባዊ ናይጄሪያ በምትገኝ ኡዮ በምትባል መንደር እየተጓዘች እያለ ልክ በዶክመንተሪ ፊልም አይታ እንደነበረው በባእድ አምልኮ ምክንያት በወላጆቹ የተጣለ የሁለት ዓመት ሕጻንን ተመለከተች።
ይህ ሕጻን በአጉል አምልኮ ምክንያት ለቤተሰቦቹ ጥሩ ዕድል አያመጣም በሚል እንዲጣል ተወስኖበት ለስምንት ወራት ያህል በሜዳ ተጥሎ ቆይቷል።
አንዳንድ ሰዎች በሚሰጡት ምግብ በሕይወት መቆየት ቢችልም አንያ በምታገኘው ወቅት ሰውነቱ በረሀብ ተጎድቶ በደንብ መንቀሳቀስ የማይችል ነበር። አንዳች ልብስ በሰውነቱ ላይ ያልነበረው ሕፃን በብርድ ክፉኛ ተጎድቶም ነበር።
በጎ አድራጊዋ አንያ ያየችው ነገር  በዶክመንተሪ ከተመለከተችው በላይ ሆነባት እና ለወራት ማንም ሊያስጠጋው ያልፈቀደውን የተጎዳ ሕፃጻን ቀርባ ውሃ ሰጠችው።
አንያ ሪንግረን ለታዳጊው ተስፋ ስትል ስም አወጣችለት። ብዙም ሳትቆይ በዚህ መጀመሪያ በታደገችው ሕፃን ስም የተስፋ ምድር የተሰኘ  የሕፃናት ማሳደጊያን ከፍታ ልክ እንደእርሱ በወላጆቻቸው የተተዉ ፤ ከቤት አውጥተው የተጣሉ  ሕፃናትን እየፈለገች ማሳደግ፣ መንከባከብ እና ማስተማር ጀመረች።
ለዚህ በጎ ተግባሯ ከተለያዩ ሀገራት እና ድርጅቶች እውቅና እና ሽልማት ያገኘች ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል እ.አ.አ በ2016 ቺልድረን ታውን የሚባለው ተቋም የሚሰጠውን የዓመቱ በጎ ፈቃደኛ ሽልማት “የፖል ሀሪስ ፊሎው” ሜዳልያ አግኝታለኝ።
በ2019 በአፍሪካ ደረጃ ማኀበራዊ ሚዲያን ለማኀበረሰብ ግልጋሎት ላዋሉ ሰዎች የሚሰጠውን ሽልማት ፤ በ2020 የናይጄሪያ የበጎ አድራጎት  ሽልማትን፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን የኦድ ፌሎው ሽልማት  እን በ2021 የዩኒቨርሳል ፖስ ፌዴሬሽን አምባሳደር በመሆን ተሹማለች።
በዚያው ዓመት የሂውማኒቲ ኢምፓክት ሽልማት፤ የላርስ ኤሪክ ፋውንዴሽን እና ከቦኤል ፋውንዴሽን የክብር ሽልማት ተሰጥቷታል ።
በ2023 የቀይ መስቀል የሰብዓዊ መብቶች ሽልማትን፤ በዴንማርክ ንጉስ ፍሬድሪክ ስም የተሰየመ የገንዘብ ሽልማት እንዲሁም ሌሎች በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችንም አግኝታለች ።
አንያ ሪንግረን በአሁኑ ወቅት መጀመሪያ ከጎዳና ላይ ያነሳችውን ተስፋን ጨምሮ ከመቶ በላይ በወላጆጃቸው የተተዉ ሕጻናትን እያስተማረች እና እየተንከባከበች ትገኛለች።
በትዳር ሕይወቷም እዚያው ናይጄሪያ ውስጥ ከተዋወቀችው የሕግ ባለሙያ ባለቤቷ ጋር በትዳር የምትኖር ሲሆን አንድ ልጅም ወልጀዋል።
በአንድ ወቅት እጅግ አሳዛኝ በሆነ መልኩ ለወራት ሜዳ ላይ ተጥሎ የተገኘው "ተስፋ" አሁን ላይ የ12 ዓመት ታዳጊ ሲሆን፤  በተመሳሳይ መልኩ ተጥለው ከተገኙ ልጆች ጋር በሚኖሩበት "የተስፋ ምድር " በተሰኘው የሕፃናት ማሳደጊያ ውስጥ እየተማረ ይገኛል።
አንያ ያላትን ንብረት ሁሉ በመሸጥ ያስፋፋችውን የበጎ አድራጎት ሥራ በማጠናከር በርካቶችን እያሳደገችም ይገኛል።

ለደቂቃ እንኳ እረፍት ሳያምራቸው፣ የግል የሚባል ሕይወት አጣጥመው ሳይኖሩ ለኢትዮጵያ ክብር ይዋደቃሉ።
ከጀግኖች አያቶቻቸው እና አባቶቻቸው የተረከቧትን ኢትዮጵያን ከነ ክብሯ እና ነፃነቷ በተሻለ ልዕልና ለልጆቻቸው ማስተላለፍ ነው ዓላማቸው።
ሁሌም ደስታቸውን እና ስኬታቸውን የሚለኩት በኢትዮጵያ ክብር እና ልዕልና ነው። በተሰማሩባቸው ግዳጆች ሁሉ በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ጠብታ ውኃ ተካፍለው ግዳጃቸውን በአኩሪ ድል ይወጣሉ።
"ከራስ በላይ ለሀገር" የሚለው ፅኑ ቃላቸው ሁሌም እንደተጠበቀ ነው። በሰላምም ሆነ በጦርነት ጊዜ ለሕዝባቸው መከታ እና መኩሪያ ናቸው - የኢትዮጵያ ወታደሮች።
ይላሉ የሠራዊቱን ሕዝባዊነት የሚገልጹት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መዝሙር የመጀመሪያዎቹ ስንኞች።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ከታደለቻቸው "ማሕፀነ ለምለም" ካሰኟት ፀጋዎች መካከል በማንኛውም ሁኔታው ውስጥ በፅናት የሚጠብቋት ልጆች እናት መሆኗን ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ መከላከያ ሠራዊቱ ዘመኑን የዋጀ ሆኖ የአባቶቹን እና የአያቶቹን አደራ በተሻለ ሁኔታ ለትውልድ ማስተላለፍ በሚችልበት መልኩ እየተዘጋጀ ይገኛል።
በፀጥታ አካላት ላይ የተደረገው ሪፎርም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ የሆነ፣ ሀገር ችግር ውስጥ በገባችበት በማንኛውም ወቅት ዝግጁ የሆነ፣ እንዲሁም በመለዮው እና በዩኒፎርሙ የሚከበር እንዲሆን አድርጎታል።
ኢትዮጵያ ያለችበት ውስጣዊ እና ውጫዊ ሁኔታ ልዩ ዝግጅት እንደሚያስፈልገው የተረዳው አመራሩ ሠራዊቱን በቴክኖሎጂም በሥነ-ልቦናም የማዘጋጀት ሥራውን በትኩረት ሠርቷል።
ተዳክሞ የነበረው አየር ኃይል እንዲጠናከር እና ዘመናዊ መሣሪዎችን እንዲታጠቅ ተደርጓል።
ሠራዊቱ በሰላም ጊዜ የልማት ዐርበኛ፣ በጦርነት ጊዜ ደግሞ ባነሰ መሥዋዕትነት የላቀ ድል እንዲያስመዘግብ ተደርጎ እየተዘጋጀ ነው።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ቀጣና ያላትን ስትራቴጂያዊ ቦታ እና የቀጣናውን ተለዋዋጭ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ዳግም እንዲቋቋም የተደረገው ባሕር ኃይል ለማንኛውም ግዳጅ ዝግጁ ተደርጓል።
ሠራዊቱ የብሔር እና የጎሣ አጥር ሳይገድበው በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ሀገሩን እያገለገለ ይገኛል።
የኢትዮጵያን ልዕልና እውን ለማድረግ ጨለማን በጣጥሶ ለሕዝቦች ብርሃንን ለመግለጥ ውድ ሕይወቱን እየከፈለም ይገኛል።
ኢትዮጵያን የሚዞሩት ታሪካዊ ባላንጣዎቿም ይህን ክንደ ነበልባልነቱን ስለሚያውቁ ነው የሚመኙትን እና የሚፎክሩትን የማይተገብሩት።
እነዚህ ስንኞች መከለከያ ሠራዊቱ በነበልባል ክንዱ የሕዝቡ የሰላም ዋስትና መሆኑን እና ሕዝቡ ደግሞ የሠራዊቱ ደጀን መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው።
የኢትዮጵያ ጠላቶች ደግሞ ኢትዮጵያን ሊተናኮሉ ባሰቡ ጊዜ የሚገጥማቸው የእሳት ነበልባል ክንድ እንደሆነ ደጋግመው እንዲያስቡበት የሚያስገድዱ ናቸው።
ይህ ሠራዊት የሰላም ዘብ ነው! ለዚህም ነው ከሀገሩ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት እና በተለያዩ ወቅቶች ችግር ውስጥ ለገቡት የአፍሪካ ሀገራት አለኝታነቱን ያረጋገጠው።
ሠራዊቱ በተሰማራባቸው የሰላም ማስከበር ግዳጆች ሁሉ ሕዝባዊነቱን እና ጀግንነቱን በተግባር ያረጋገጠ የኢትዮጵያም የአፍሪካም መከታ ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ትላንትም ሆነ ዛሬ ጀግንነቱን ጠብቆ ኢትዮጵያን በደሙ እያፀና የመጣ፣ ነገም ይህንኑ በላቀ ግዳጅ አፅንቶ የሚቀጥል እውነተኛ የሕዝብ ልጅ ነው።

በከተማ የሚከናወኑ የተለያዩ የበጎ ፍቃድ ሥራዎች ላይ ግንባር ቀደም ሆና ትሳተፋለች።
ሙኒራ በከተማዋ ሁለቱም ኩላሊቶቹ ሥራ አቁመው የነበረውን የወጣት ማህዲ ተኮላን ታሪክ ትሰማለች።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ለኩላሊት እጥበት ከፍተኛ ወጪኝ ሲያወጣ የነበረው ወጣት ደግሞ የከፋ ችግር ላይ ነበር።
ቤተሰቦቹ ያላቸው ንብረት እየሸጡ ለኩላሉት እጥበት እና ለተለያዩ ሕክምናዎች ሲያውሉ ቆይተዋል።
በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥም ለኩላሊት ተማሚው የሕክምና ወጪ የሚውል ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ በማሰባሰብ በጎ ተግባሯን ማጠናከርም ችላለች።
አሁን ላይ የታማሚው እናት ኩላሊት ተመርምሮ ለልጃቸው ሕክምና ኩላሊታቸውን መሰጠት እንደሚትችሉ በሐኪሞች ስለተነገራቸው ወደ ሕንድ ሀገር ሄደ ንቅለ ተከላ ለማካሄድ ተጨማሪ ድጋፍ እየጠየቁ ይገኛሉ።
ለኩላሊት ንቅለ ተከላው 5.5 ሚሊዮን ብር የሕክምና ወጪ ስለሚያስፈልግ ይህ ገንዘብ ከአቅማቸው በላይ የሆነው የታማሚው ቤተሰቦች እጃቸው ለእርዳታ ዘርግተዋል።
በአፋር ክልል ከተለያዩ አከባቢዎች የሚገኙ ዜጎች የዚህን ወጣት ሕክምና ወጪ በመሸፈን ከፈጣሪ በታች የወጣቱን ሕይወቱን ለማትረፍ ድጋፍ እያቀረቡም ይገኛል።
ሙኒራ ኢብራሂምም "የማህዲ እናት ልጄን አድኑልኝ የሚል ተማጽኗቸውን ዛሬም አስታውሳለሁ እና ወጣቱ ድኖ እስከማየው ድረስ የበጎ ፈቃድ ሥራውን አላቋርጥም" ስትል ተናግራለች።

የአፍሪካ ትልቁ ስለሆነው የሕዳሴ ግድብ ከኃይል አመንጭነቱ ባሻገር ስላለው ዘርፈ ብዙ ጥቅም በአሜሪካ የሲቪል መሐንዲሶች ማህበረሰብ ድረ-ገፅ ሰፋ ያለ ትንታኔ ቀርቧል።
በድረ-ገፁ በፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲ የመሬት እና የአካባቢ ጥበቃ ክፍል የውኃ ሀብት ምህንድስና ተመራማሪው አሰፋ መለሰ (ዶ/ር) እና በሂዩስተን የሚገኘው ኢንቴክ ሲቪል መሐንዲሶች ተቋም የውኃ ሀብት አጠቃቀም አስተባባሪው አለማየሁ ገብርኤል ሰፋ ያለ ጽሑፍ አስነብበዋል።
በጽሑፋቸውም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተቀዳሚ ተግባሩ ከሆነው ኃይል ማመንጨት በተጨማሪ በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት አስቀምጠዋል።
ግድቡ ለጎርፍ መቆጣጠሪያ መለኪያ፣ የጥቁር ዓባይን ፍሰት ለመቆጣጠር እና በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት በተለይም በሱዳን ላይ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን አውዳሚ የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ይረዳል ብለዋል ምሁራኑ።
የግድቡ ውኃ የመያዝ አቅም በመስኖ የግብርና ምርታማነትን ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃልም ያሉ ሲሆን፤ ይህም ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የቀጣናውን ሀገራት ጭምር የሚጠቅም መሆኑን ገልጸዋል።
በኢኮኖሚው ዘርፍም ስንመለከተው ግድቡ ኢትዮጵያ ኃይልን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ገቢዋን እንድታሳድግ ትልቅ እድል የፈጥርላታልም ብለው፤ ይህም ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገቱ ተጨማሪ ማስፈንጠሪያ ሊሆን እንደሚችልም ነው ያነሱት።
ከምንም በላይ ደግሞ ከሀገራዊ እይታ አንጻር ግድቡ የኢትዮጵያውያን ኩራት እና በራስ የመተማመን ምልክት ሆኖ የቆመ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም አገሪቷ ራሷን ችላ ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን የማከናወን እና ፋይናንስ የማድረግ አቅም እንዳላት ያሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ይህም ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ታዳጊ ሀገራትን ጭምር የውጭ ዕርዳታ ላይ የተመረኮዙ የልማት ሥራዎችን ቀስ በቀስ በመላቀቅ በራስ አቅም ወደ ማልማት የሚያሸጋግር ድልድይ እንደሆነም ምሁራኑ በጽሑፋቸው አስነብበዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሂደት የግድብ ጉዳይ ብቻ አይደለም የሚሉት ምሁራኑ፤ ግድቡ በዓለም ላይ ካሉት እጅግ ታሪካዊ የወንዞች ተፋሰሶች አንዱ በሆነው የዓባይ ተፋሰስ አካባቢ ቀጣናዊ ትብብር፣ ዘላቂ ልማት እና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ላይ ትልቅ ሚና የሚኖረው መሆኑን አስምረውበታል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ የተገነባው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከአፍሪካ ትልቁ የውኃ ኃይል ማመንጫ ሲሆን፤ ለኢትዮጵያ ከሚያበረክተው የኤሌክትሪክ ኃይል በተጨማሪ በዓባይ የታችኛው ተፋሰስ አካባቢ የሚገኙ ሃገራትን ከጎርፍ አደጋ የሚጠብቅ ብሎም የተፋሰሱን የውኃ ብክነት የሚቀንስ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
እ.ኤ.አ. በ2011 ፕሮጀክቱ መገንባት ሲጀምር ከ 30 በመቶ ያነሱ ኢትዮጵያውያን ብቻ የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ ነበሩ። ይህም የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት እና የዜጎችን ሕይወት በእጅጉ የጎዳም ነው።
ግድቡ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ከእጥፍ በላይ እንደሚያሳድግ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ይህም ኢትዮጵያን የኃይል እጥረት ካለባት ሀገር ወደ ምስራቅ አፍሪካ ዋና የኃይል አቅራቢነት እንደሚያሸጋግራት ይጠበቃል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከዲዛይን ጀምሮ እስከ ግንባታ ብሎም ጂኦፖለቲካዊ ውዝግቦችን ጨምሮ በርካታ ፈተናዎችን አልፎ፤ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ይመረቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የዓባይ ወንዝን ለኃይል ማመንጫነት የመጠቀም ሀሳብ በኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ሀሳብ ሆኖ የቆየም ነው። ይሁን እንጂ ቀደም ባሉት ጊዜያት እንዲህ ያለ ትልቅ ፕሮጀክት ለመገንባት የሚያስችል የቴክኖሎጂም ሆነ  የገንዘብ አቅም ሀገሪቱ አልነበራትም።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዘመናዊ ገጽ የተገለጠውም ለበርካታ አስርት ዓመታት የተደራጁትን በርካታ ጥናቶችና ውይይቶች ይዞ ነው።

ምንም እንኳን ናይጄሪያ በ36 ክልሎች ውስጥ 275 ዩኒቨርሲቲዎች እና በርካታ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ቢኖሯትም፣ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር በየዓመቱ እየቀነሰ ነው።
በዚህ ዓመት ብቻ ከ275 ዩኒቨርሲቲዎች መካከል 199ኙ በጣም ጥቂት ተማሪዎች ሲቀበሉ፣ 34ቱ ደግሞ አዲስ ተማሪዎችን አልተቀበሉም። በአሁኑ ጊዜ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከሚያጠናቅቁ ናይጄሪያውያን ተማሪዎች መካከል ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡት 12 በመቶ ብቻ እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።
•  የትምህርት ጥራት ማነስ እና የገንዘብ ችግር:- ተማሪዎች ራሳቸው እንደገለፁት፣ የትምህርት ጥራት መጓደል እና የገንዘብ ችግር በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የመማር ማስተማር ሂደቱን እያደናቀፈ ነው።
•  የሴቶች ተሳትፎ ማነስ:-  በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ውስጥ ወደ ከፍተኛ ትምህርት የሚገቡ ተማሪዎች መካከል ሴቶች የሚይዙት ድርሻ 21 በመቶ ብቻ ነው። ይህ ችግር በናይጄሪያ ባለው የጸጥታ ችግር     እየተባባሰ መጥቷል።
•  ከፍተኛ የትምህርት ክፍያ:- የግል ዩኒቨርሲቲዎች በዓመት እስከ 2,400 የአሜሪካ ዶላር ስለሚያስከፍሉ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ልጆቻቸውን የማስተማር እድል አጥተዋል።
•  ወደ ውጭ ሀገር መጓዝ፦ ብዙ ናይጄሪያውያን ተማሪዎች የትምህርት ጥራትን እና ሌሎች ችግሮችን በማምለጥ ወደ ውጭ ሀገራት ለመማር ይሄዳሉ። በአፍሪካ ከሚመጡት የውጭ ተማሪዎች ውስጥ ናይጄሪያውያን ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ።
•  የጸጥታ ችግር፦ የትምህርት ጉዳዮች ባለሙያ የሆኑት ሸሪፍ ጋሊ ኢብራሂም እንደገለፁት፣ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተማሪዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ እንቅፋት ፈጥረዋል።
ናይጄሪያዊያን የትምህርት ባለሙያዎች እንደተናገሩት፣ የመንግሥት ውሳኔ ትምህርትን ከፖለቲካ እና ከሃይማኖት ጣልቃ ገብነት ነጻ ማድረግ ነው። የመንግሥት ውሳኔው በቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት ውስጥ ምንም አዲስ የፌደራል ዩኒቨርሲቲ እንደማይገነባ ነው። ይህም አሁን ያሉትን ዩኒቨርሲቲዎች በማጠናከር እና የትምህርት ጥራትን በማሻሻል ላይ ትኩረት ለመስጠት ታስቦ ነው።
ይህ የመንግሥት ውሳኔ ግን በዘርፉ ምሁራን መካከል ልዩነት ፈጥሯል። አንዳንዶች የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ የሚረዳ እርምጃ ነው ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ ስር የሰደዱትን የጸጥታ እና ሌሎች ችግሮች አይፈታም በሚል ተችተውታል።
የትምህርት ፖሊሲ ባለሙያ የሆኑት አዴኒይ አቢኦዱን እንደገለፁት፣ የናይጄሪያን የትምህርት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ሚዛናዊ እና በጥንቃቄ የታሰበበት መዋቅራዊ ለውጥ ያስፈልጋል። ባለሙያዎቹ ትምህርት ቤቶችን ደህንነት ማረጋገጥ፣ የትምህርት ተደራሽነትን ማስፋት እና የክፍያ ዋጋን ተመጣጣኝ ማድረግ የመማር ማስተማር ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን ወሳኝ መሆኑን አክለዋል።

ሩሲያ ከባይኮኑር ኮስሞድሮም ወደ ዓለም አቀፍ የጠፈር ጣቢያ ያመጠቀችው ፕሮግረስ ኤምኤስ-32 የጭነት መንኮራኩር በተሳካ ሁኔታ ወደ ተዘጋጀላት ምህዋር መግባቷን የሩሲያ መንግስታዊ የጠፈር ኮርፖሬሽን ሮስኮስሞስ አስታውቋል።
ሮስኮስሞስ ባወጣው መግለጫ ላይ "የመንኮራኩሩ ወደ ተዘጋጀለት ምህዋር መግባት፣ ከሮኬቱ ሶስተኛ ክፍል መለየቱ እና የአንቴናዎችና የፀሐይ ኃይል ሰሌዳዎች መዘርጋት በተያዘለት እቅድ መሰረት ተፈጽሟል" ብሏል።
የጭነት መንኮራኩሩ ቅዳሜ ዕለት በሞስኮ ሰዓት አቆጣጠር 20:27 ላይ ከዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ የሩሲያ ክፍል ዝቬዝዳ ሞጁል ጋር እንደሚጣበቅ ይጠበቃል።
እንደ ሮስኮስሞስ ገለጻ፣ መንኮራኩሩ የመጠጥ ውሃ፣ ለጣቢያው የሚያገለግል ነዳጅ፣ የጣቢያውን ከባቢ አየር ለመሙላት የሚያገለግል አየር እና የሳይንስ መሳሪያዎችን ጨምሮ ከ2.5 ቶን በላይ ጭነት ወደ ጣቢያው ያደርሳል።

ጆርጂያ ሜሎኒ እ.አ.አ. በጃንዋሪ 15 ቀን 1977 በሮም ጣልያን ነው የተወለዱት።
ወላጅ እናታቸው አና ፓራቶሪ ከባለቤታቸው ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት በመለያየታቸው በወቅቱ የ3 ዓመት ሕፃን የነበረችውን ጆርጂያን እና ታላቅ እህታቸውን አርያናን ለማሳደግ ከባድ መስዋዕትነት መክፈል ነበረባቸው።
በዚህ አይነት መልኩ ሮም ውስጥ በምትገኝ ትንሽ ቤት ውስጥ ከልጅነታቸው አንስቶ በችግር ያደጉት ጆርጂያ ሜሎኒ ከፖለቲካው ዓለም ጋር መተዋወቅ የጀመሩት ገና በ15 ዓመታቸው ነበር።
የጣሊያን ሶሻል እንቅስቃሴ (Italian Social Movement -MSI) የተባለውን የፖለቲካ ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ በመቀላቀል  "ሀ" ብለው ፖለቲካውን ተቀላቅለዋል።
ሆኖም ወንዶች የፖለቲካውን መድረክ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ በተቆጣጠሩበት ቦታ እና ጊዜ የጆርጂያ ሜሎኒን የፖለቲከኛነት ጅማሮ ብዙ ሰዎች በበጎ አልተቀበሉትም ነበር። አንዳንዶቹም በግልፅ ቦታቸው ይህ እንዳልሆነ ይነግሯቸው ጀመር።
ታዳጊዋ ጆርጂያ እንዲህ አይነት አስተያየት ለሚሰጧቸው ሰዎች እየሄዱበት ያለው መንገድ ትክክለኛ እንደሆነ እና አንድ ቀን ጣልያንን እንደሚመሩ ይነግሯቸው እንደነበር የታሪክ ሰነዳቸው ያስረዳል።
ገና በለጋ እድሜያቸው ፓርቲውን ሲቀላቀሉ አንድ ጣልያናዊ ‘አንቺ ልጅ ነሽ ወደቤትሽ ብትሄጂ የተሻለ ነው’ ይላቸዋል፤ ያኔ ታዲያ የጆርጂያ ምላሽ ‘እዚህ የተገኘሁት ሀገሬን ለመምራት ነው’ የሚል ነበር።
ጆርጂያ ችሮችን በመቋቋም ከትምህርታቸው ጎን ለጎን አባል በሆኑበት የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ እየተሳተፉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዲፕሎማ አጠናቀቁ። ይሁንና በወቅቱ በአቅም ማነስ ምክንያት የኮሌጅ ትምህርታቸውን መግፋት አልቻሉም።
ሆኖም ችግሩ አላማዬ ብለው ከያዙትነገር ሊያግዳቸው አልቻለም። እናም ያለ አባት ያሳደጓቸውን እናታቸውን  ለማገዝ የሙዚቃ ሲዲዎችን መሸጥ ጀመሩ።
አዘውትረው ያዳምጡት በነበረውት የማይክል ጃክሰን እና ሌሎች  የእንግሊዝኛ ሙዚቃዎች አማካኝነት እንግሊዝኛ ቋንቋን ያለ አስተማሪ መማር ችለዋል።
በአስተናጋጅነት እንዲሁም ሞግዚት ሆኖ በመስራት ሕይወትን ለማሸነፍ እና ቤተሰባቸውን ለመርዳትም ጥረት አድርገዋል። ከዚህ በሚተርፋቸው ጊዜም አባል በሆኑበት ፓርቲ በንቃት መሳተፋቸውን ቀጠሉ።
በፓርቲ ተሳትፏቸው የውይይት ወቅት በበሳል ሀሳብ አፍላቂነታቸው እና በተናጋሪነታቸው ይታወቁ ነበር።
እንዲህ እንዲህ እያለ የሄደው የጆርጂያ ሜሎኒ ሕይወትና የፖለቲካ ጉዞ እያደገ በተለያዩ ሃላፊነቶች መመደብ ችለዋል።
እ.አ.አ. በ1996 ዩዝ አክሽን የተባለውን ብሔራዊ የተማሪዎች ንቅናቄ መምራት ችለዋል።
በ1998 የሮማ ግዛት ካውንስል ሆነው ተመረጡ፣ ጆርጂያ ሜሎኒ ወደዚህ የመጀመሪያዋ በሆነው ይፋዊ የፖለቲካ ሚና መሳተፍ ሲጀምሩ ዕድሜያቸው ገና 21 ነበር።
ከዚያም በ2008 የጣልያን የታችኛው ምክር ቤት የፓርላሜንት አባል በመሆን ተመረጡ።
ጆርጂያ ሜሎኒ በሙሉ አቅምና ጉልበታቸው በፖለቲካው መሳተፋቸውን ቀጥለው እ.አ.አ. በ2008 ልክ በ31 ዓመታቸው በወቅቱ የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩት በሲልቪዮ በርልስኮኒ አማካኝነት የጣልያን የወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተመረጡ።
በሚኒስትርነት ቦታው ካገለገሉ በኋላም እ.አ.አ. በ2012 የጣልያን ወንድማማቾች ፓርቲ የተሰኘውን የፖለቲካ ድርጅት አቋቋሙ።
አዲሱ ፓርቲ እንደተቋቋመ በሕዝብ ዘንድ በፍጥነት ተቀባይነት አላገኘም ነበር። ሆኖም ህልማቸውን እና ለአገራቸው ያላቸውን ብሩህ ራዕይ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለሕዝቡ በማስረዳት ፓርቲው በሕዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት እየጨመረ እንዲሄድ ማድረግ ቻሉ።
ጆርጂያ ሜሎኒ በወንዶች ብቻ ተይዞ በቆየው የጣልያን ፖለቲካ መድረክ ላይም እያገዘፉ መጡ።
ከፊት ለፊታቸው የነበሩ የተለያዩ መሰናክሎችን በማለፍ ራሳቸውን በእውቀት እየገነቡ ወደፊት መገስገስ የጀመሩት ጆርጂያ ሜሎኒ፤ የፖለቲካ ጉዟቸው በስኬት ላይ ስኬትን እያስገኘ በ2022 በተደረገው ብሔራዊ ምርጫ በ45 ዓመታቸው የመጀመሪያዋ የጣልያን ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተመረጡ።
ጆርጂያ ሜሎኒ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ከያዙ በኋላ በተለያዩ ዘርፎች ስኬትን ማስመዝገብ መቻላቸው በሕዝብ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ጨምሮታል።
ደጋፊዎቻቸውም ጆርጂያ ሜሎኒ አገሯን የምትወድ፣ የቤተሰብ ሃላፊ፣ ማኀበራዊ እሴቶችን የምታስከብር እና በአውሮፓ መድረኮች የጣልያን ድምፅ መሆን የቻለች ሲሉ ያወድሷቸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለአፍሪካውያን ጭምር ኩራት መሆኑን የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ዜጎች ገለጹ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚጠቀሱ 10 ታላላቅ ግድቦች አንዱ የሆነው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ በራስ አቅም መገንባቱም በአህጉሪቱ ትልቅ መነሳሳትን የፈጠረ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በኢንቴቤ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ (ኡጋንዳ) የበረራ ተቆጣጣሪ የሆኑት ዛም ዛም፥ ግድቡ ያለ አንዳች የውጭ ድጋፍ መገንባቱ የሚያኮራ ነው ብለዋል።
ዛም ዛም ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ግድቡ ቀጣናዊ ትስስርን በማሳለጥ ረገድ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልጸው፤ የኃይል አቅርቦቱ በቀጣናው ያለውን የኢንዱስትሪ ልማት እንደሚያፋጥነው አክለዋል።
በኬንያ የአካባቢ፣ አየር ንብረት ለውጥ እና ደን ልማት ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለውጥ ምክትል ዳይሬክተር ሚካኤል ኦኩሙ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደዚህ ዓይነት ግዙፍ እና አስደናቂ ግድብ መገንባቱ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

ሀገራት ሁሉ ስደተኞችን ይጠየፋሉ ብሎ መደምደም አይቻልም፤ አንዳንዶች የሚያስፈልጋቸውን የሰው ኃይል በብዙ አማራጮች ያገኛሉ፤ ከእነዚህም መካከል በስደት ወደ ሀገራቸው የሚሄዱትን ሰዎች አቅም መጠቀም ነው።
በእርግጥ ሁሉም ሀገራት የራሳቸውን ብሔራዊ ጥቅም መሠረት አድርገው የሚሠሩ ቢሆንም ስደተኞችን የሚጠየፉ መኖራቸውም የሚካድ አይደልም። ለዚህም ነው “ሁሉም በሀገር” የሚሉ ብሂሎች በርከት ብለው የሚሰሙት።
“ምድር የተፈጠረችው ለሰው ልጆች መኖሪያነት ነው” የሚሉ ፈላስፎች፣ ሰዎች የትም ሄደው በፈለጉት ሁኔታ ውስጥ እንዲኖሩ ማቀንቀናቸው ተፈጥሯዊ ቢሆንም ይህን ሕግ ግን በሰው ሠራሽ የየሀገራት መመሪያዎች መቀየራቸው እውነት ነው።
በስደተኞች ጉዳይ ዓለም በአንድ ቋንቋ ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን ቢናገርም ሀገራት ግን በጉዳዩ ዙሪያ መፍትሔም ሆነ ቢሆን የሚሉት ከሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅም አንጻር ነው።
ለዚህም ነው በስደት ጉዳይ አንድ ወጥ መፍትሔ አመላካች ፍኖተ ካርታ ማግኘት የሚቸግረው።
እዚህ ላይ አውሮፓውያኑ “ከአፍሪካ የሚነሣ ስደት እኛን ያጠፋናል” ብለው እንደሚሰጉ ሁሉ አፍሪካውያን ከአውሮፓ የሚነሣ የጥፋት እሳቤ ያሳስባቸዋል። እናም የጋራ መፍትሔ ሳይሆን የጋራ ችግር ብቻ ይዞ ዓለም እንዲኖር የተከፈለበት ይመስላል።
በአፍሪካ በተለያዩ ወቅቶች ወደ አውሮፓ የሚደረጉ ጉዞዎች በሕገ ውጥ ስደት ሰንሰለት ውስጥ መያዛቸው ደግሞ “ለነፍስ ነጋዴዎች” በሰው ነፍስ መነገድ ውኃ በብርጭቆ እንደመጠጣት ቀላል ሆኖላቸዋል።
በዚህ የሕገወጥ ጉዞ ውስጥ ከግለሰብ እስከ ትላልቅ ተቋማት የሚሳተፉበት በመሆኑ ለአንዳንድ ሀገራት ችግሩን ለማስቆም አዳጋች መልክ እንዲኖረው አድርጎታል።
በዚህ መሐል ውስጥ ነፍሳቸውን አስይዘው ያላቸውን ገንዘብ ከፍለው ጉዞ የሚጀምሩ አፍሪካውያን ሕይወታቸውን እያጡ ነው የሚባል ዜና በተደጋጋሚ ቢሰማም ጆሮ ሰጥቶ ይህ ነገር ይብቃኝ የሚል ሳይሆን በዚሁ መንገድ የሚጓዝ የትውልድ አካል መኖሩ ደግሞ አሳሳቢ ነው።
በአራቱም ማዕዘናት ባሉት የመውጫ መንገዶች ሁሉ በሕገወጥ መንገድ በተለይ ወደ አውሮፓ የሚጓዙ ሁሉ የሚደርስባቸው መከራ እና እንግልት የሚነገር ባይሆንም ከሞት መትረፍ ዕድል በሆነበት መንገድ የማይታይ እና የማይሰማ ታሪክ የለም።
ከእነዚህ ታሪኮች እና የሕይወት ገጠመኞች ውስጥ የተረፉ ድምጾች የሚነግረን ተመሳሳይ ጎዳና አንድ ዓይነት ሞት እና የሕይወት ዘመን ጠባሳን ነው። እዚህ ላይ በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2023 የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ በሕገወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ ለመጓዝ ያሰቡ ድምጾች ሁሌም ይነሣል።
በዚህ ወቅት 101 ሴናጋላውያንን የያዘችው አነስተኛ ጀልባ አቅጣጫዋን ወደ ካናሪ ደሴቶች በማድረግ ጉዞዋን ጀመረች።
ከእንጨት በተሠራችው አነስተኛ ጀልባው ውስጥ በአብዛኛው ወጣት ወንዶችና ታዳጊዎች ነበሩበት። የሁሉም ህልም የስፔን ግዛት ወደሆነው ካናሪ ደሴት መድረስ ነው። ጉዟቸው አንድ ሳምንት ብቻ  እንደሚወስድ በተነገራቸው መሠረትም ለዚህ ጉዞ የሚሆናቸውን ሩዝ እና ለመጠጥ የሚሆን ውሃ ይዘዋል።
ሴኔጋላውያኑ መንገደኞች በዚህ አደገኛ የሆነ የባሕር ጉዞ ሊያጋጥማቸው ከሚችለው አደጋ ይልቅ በስፔን ወይም በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ሊኖራቸው ስለሚችለው የተሻለ ሕይወት ብቻ እያሰቡ ጉዟቸውን ቀጠሉ።
ሆኖም ከጥቂት ቀናት የባሕር ጉዞ በኋላ ለዚህ አይነት አስቸጋሪ ጉዞ ያልተሠራችውና ከመጠን በላይ ጭነት የተሸከመችው ጀልባ ሞተሯ መበላሸት ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ለባሕር ጉዞ ዋና አስፈላጊ መሳሪያ የሆነው አቅጣጫ ጠቋሚ የጂፒኤስ መሳሪያ ስራ አቆመ።
በአትላንቲክ ውቅያኖስ ያለአቅጣጫ አመላካች ኮምፓስ መጓዝ ፈፅሞ የማይታሰብ ነገር በመሆኑ ጉዟቸው ወደማይሆን አቅጣጫ ማምራት ያዘ። ሞተሯ ብልሽት የገጠመው ጀልባ ንፋሱ ወደሚወስዳት መሄድ ጀመረች።
ሰባት ቀን ብቻ እንደሚፈጅ የታሰበው ጉዞ የማይሆን ሆነ። ቀኑ ይመሻል ሌሊቱ ይነጋል  ፀሐይና ብርድ እየተፈራረቀባቸው ወደየት እንደሚጓዙ ቀርቶ የት እንዳሉም ማወቅ ተሳናቸው። በዚህ ሁኔታ እያሉም ለሳምንት የያዙት ምግብና ውሃ አለቀ።
በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ  ያላንዳች ምግብና ውሃ፣ ወጀብና ነፋስ በሚወስዳቸው አቅጣጫ  እየሄዱ ከቆዩ በኋላ አንዳንዶቹ አዕምሯቸውን መሳት ጀመሩ። ጥቂት የማይባሉት በተስፋ መቁረጥ ራሳቸውን ወደ ውቅያኖሱ ወረወሩ። ህመም፣ ረሀብ፣ ስቃዩና መከራው ከሚችሉት በላይ የሆነባቸው በእንጨት ጀልባቸው ላይ ሆነው ለዘለዓለሙ አንቀላፉ።
በሕይወት የተረፉት ቀሪዎቹ በስቃይና በተስፋ መቁረጥ በሞት የተለዩትን የጉዞ ጓደኞቻቸውን አስከሬን ወደ ውቅያኖሱ በመጨመር ተሰናበቷቸው። በወዳጆቻቸው ሀዘን ለማልቀስ የሚያስችል አቅም እንኳን አልነበራቸውና በዝምታ አነቡ።ነገ የእነሱም ዕጣ-ፈንታ ምን እንደሆነ የማያውቁት  የተሻለ ሕይወት ፈላጊ ወጣቶች  የሳምንቱ ጉዞ ሁለት ሳምንት ወር እያለ ለ36 ቀናት በባሕር ላይ ጠፍተው ከረሙ።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ለ36 ቀናት ጠፍታ የነበረችውን ጀልባ  ሲያገኙ  ሴኔጋል አንድ መቶ አንድ  ሆነው ተነስተው ቀስ እያሉ እያለቁ የቀሩት 38 ሰዎች ብቻ ነበሩ። እነሱም በውቅያኖስ ጨዋማ ውሃ ፊታቸው ተቃጥሎ በፀሐይና ብርድ ተጎሳቁለው የደከሙና በከፍተኛ ሁኔታ የታመሙ ነበሩ። ይህም ሆኖ ዋናው ጥሩ ነገር እና ዕድለኛ ሆነው ነፍሳው ብቻ አለች።
በዚህ ሁኔታ በሕይወት ከተረፉት ውስጥ አንዱ ሲናገር፦ “ቤተሰቦቻችንን ተሰናብተን  ከሴኔጋል ስንነሣ የሚታየን ጉዟችን ተሳክቶ በአውሮፓ ሀገራት ስለሚያጋጥመን  ብሩህ ሕይወት ብቻ ነበር። እንዲህ አይነት አስፈሪ ቅዠት የሚመስል ነገር እንደሚያጋጥመን ብናውቅ ከሀገራችንም ባልተነሣን ነበር። በዚህ አደጋ ከሞቱት ውስጥ አንዱ የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ አብሮኝ የተሰደደው ጓደኛዬ ይገኝበታል። የመጨረሻ እስትንፋሱን ሲወጣም እያየሁት ነበር። ብዙ ህልም ያላቸው ሰዎች በሞት አጥተናል። ምናልባት እኔም በሕይወት የተረፍኩት ይህንን አሳዛኝ ክስተት ለሌሎች እንድመሰክር ይሆናል።” በማለት በሕገ-ወጥ መልኩ ስደትን ለሚያስቡ ሰዎች የጉዞውን አስከፊነት ተናግሯል።
በዚህ አይነት ሕይወትን ለአደጋ የሚያጋልጥ ጉዞ ውስጥ አልፈው የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ የሚሰደዱ አፍሪካውያን ቁጥር ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ በመሄዱ የአደጋው ተጋላጭ ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨምሯል።
እንደ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅ (IOM) መረጃ ከ2014 ጀምሮ ከሀምሳ ሺህ በላይ አፍሪካውያን በሕገወጥ መንገድ ከሀገር ለመውጣት በሚሞክሩበት ወቅት ሕይወታቸውን አጥተዋል።
የዚህ የሕገወጥ ስደት ሰለባ ሆነው በተለያየ ጊዜ  ክቡር ሕይወታቸውን በባሕርና በመንገድ ላይ ታጣቂዎች እያጡ ከሚገኙ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ዜጎች መሀከል ኢትዮጵያውያንም ይገኙበታል።
ከቀናት በፊትም በዚሁ አይነት ሁኔታ ወደ ሳዑዲ ለመጓዝ አስበው ጉዞ የጀመሩ 154 ኢትዮጵያውያንን የጫነች ጀልባ በየመን የባሕር ዳርቻ በመስጠሟ በሕይወት ማግኘት የተቻለው 12 ሰዎችን ብቻ ነበር።
ከዓመታት ጀምሮ እስካሁንም በቀጠለው በዚህ ያልተዘጋው የሞት መንገድ ሊያጋጥማቸው ከሚችለው የተሻለ ሕይወት ይልቅ አደጋው እንደሚያመዝን ቢታወቅም ከእለት ወደ እለት ቁጥሩ እየጨመረ ይገኛል።
መንግሥት ይህንን ሁኔታ ለመቀነስ እያደረገ ባለው ጥረት ከውጭ ሀገራት ጋር ህጋዊ የሥራ ስምምነት ውል በመፈራረም ኢትዮጵያውያን ሥራ ፈላጊዎች በህጋዊ መልኩ መስራት እንዲችሉ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ይገኛል።
በዚህም መሠረት ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬት፣ ከዮርዳኖስ፣ ከሊባኖስ፣ ከኳታር እና ከኩዌት መንግሥታት ጋር የሁለትዮሽ የሥራ ስምሪት ስምምነት በመፈራረም ወደ ሥራ እንዲገባ የተደረገ ተደርጓል።
በ2014 ዓመት 69 ሺህ 718፣ በ2015 ዓመት 102 ሺህ 076፣ በ2016 ዓመት 345 ሺህ 167 እንዲሁም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 503 ሺህ 173 ዜጎች መንግሥት በዘረጋው ህጋዊ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ስርዓት ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር መረጃዎች ያመላክታሉ።
በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት መጓዝ ክቡር ሕይወትን ከመታደግ ባለፈ ትናንሽ ችግሮች እንኳን ቢከሰቱ ለመፍታት ብዙ ሰርቀትን መጓዝ አይጠይቅም። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ከሰሞኑ በሳዑዲ አረቢያ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ተፈጽሞባት ካሳ ያገኘችው መካ መሃመድ አራጋው ነች።
መካ ወደ ሳዑዲ በህጋዊ መንገድ ከሄደች በኋላ ያጋጠማትን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያየው በሳዑዲ የኢትዮጵያ ኤምባሲው ጉዳዩን በቀላሉ አልተመለከተውም።
እዚህ ከኢትዮጵያ ወደ ሳዑዲ ጉዞዋን በሕጋዊ መንገድ ያደረገችው መካ መሃመድ መሉ መረጃዋ እሷ ሳዑዲ ከመድረሷ በፊት ለኤምባሲው ደርሶት ስለነበር ጉዳዮን ወደ ፍትህ በመውሰድ ነበር የጀመረው።
ያቀረበውን ክስ መሠረት አድርጎ የሳዑዲ አረቢያ የጸጥታ አካላት ክትትል በማድረግ በመካ መሃመድ ላይ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ሲፈጽሙ የነበሩትን ሁለት ሴቶች በቁጥጥር ሥር በማዋል ተበዳይ መካ መሀመድን ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ኢምባሲ ቅጥር ጊቢ እንድትመለስ ማድረግ ችሏል።
በሂደቱም የመካ መሀመድ አሰሪዎች የፈጸሙትን ኢ-ሰብዓዊ ተግባር በማመናቸው እና በመፅፅታቸው በቤተሰብ ደረጃ በድርድር እንዲያልቅ ለኢምባሲው ተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበዋል።
መካ መሀመድ ጉዳዩ በሽምግልና እንዲያልቅ ተጠይቃ በመፍቀዷ 20 ሺህ የሳዑዲ ሪያል የሞራል ካሳ እንዲከፈላት በማድረግ እርቅ ማውረድ እና ፍላጎቷ የነበረው ወደሀገር ቤት የመመለስ ጥያቄዋን ኤምባሲው አመቻችቶላታል።
እዚህ ላይ ትልቁ ቁም ነገር እሷ እንኳን ወደ ኤምባሲ መሄድ ባታስብ እና ባትችል ኤምባሲው ችግሯን አይቶ እንዳያልፍ ብሎም ያለችበትን በሂደትም ለማወቅ እንዲችል ቀድሞውኑ መረጃዋ ስላለው ጉዳዮን በቀላሉ ፍትህ ለማሰጠትም እንዲችል አድርጎታል።
በህጋዊ መንገድ መሄድ ጠቀሜታው ይህ ነው ይህ ነው ተብሎ የሚተነተን አይደለም። ምክንያቱም እንደ መካ መሀመድ ሁሉ ከብዙ ችግር ውስጥ ከመውጣት እስከ ሕይወትን መታደግ የደረሰ ብዙ ነው። ለዚህም ነው መግሥት ዜጎች በሀገራቸው ሰርተው መለወጠን ከዚህ ሲያልፍ ደግሞ በህጋዊ መንገድ ብቻ የሚደረግ ጉዞን ነው የሚደግፈው።
መደገፍ ብቻም አይደለም ህጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪቶችን ለማድረግ የሚያስችሉ ስምምነቶችን ከተለያዩ ሀገራት ጋር በማድረግ ይፋ አድርጓል።
ይህም በመሆኑ መንግሥት በቀጣይ የስራ ስምሪት መዳረሻዎችን ለማስፋት የሚያደርገው ጥረት እንዳለ ሆኖ እስከዛው ግን ዜጎች መንግሥት ካወጣው ህጋዊ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ውጭ በሌሎች በተሳሳቱ መረጃዎች ተታለው ባለመሄድ ክቡር ሕይወታቸውን ከአደጋ መጠበቅ ይገባቸዋል።

በኢትዮጵያ የቴአትር እና የፊልም ታሪክ ትልቅ ዐሻራን ያሳረፉት፤ ሀገራቸውን በሙሉ ልባቸው የሚወዱት እና ያገለገሉት ብሎም በነፈሰው ሳይነፍሱ ከሀገራቸው ጎን የቆሙት አርቲስት ደበበ እሸቱ ከዚህ ዓለም በሞት  ተለይተዋል።የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴዔታ ነብዩ ባዬ ሀዘናቸውን በገለጹበት ወቅት "አርቲስት ደበበ የሀገር ወዳድነት ማሳያ ብቻ ሳይሆን፤ ያለውን ልምድና ዕውቀት ያለስስት ለወጣቶች ያጋራ ነው። ሲሉ ተናግረዋል።በዓለምአቀፍ ፊልሞች ላይ የተሳተፉት ኢትዮጵያን እና አፍሪካን በጥበቡ ዓለም ተቋማት የወከሉት የበጎ ሥራ አምባሳደሩ፤ ሕዝብ ነጻ ለማውጣት ወደ ፖለቲካም የገቡት አርቲስት ደበበ እሸቱ እንዲህ ይታወሳሉ፦በ1934 ዓ.ም የተወለዱት አርቲስት ደበበ እሸቱ፤ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። አርቲስት ደበበ የቴአትር ጥበብ ጅማሮአቸውም በዚሁ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት እንደሆነ ይነሳል።አርቲስት ደበበ እሸቱ ቴአትር የሕይወት ዘመናቸው ጥሪ መሆኑን በጊዜው እንዳላስተዋሉም በቃለ መጠይቆች ላይ ተናግረዋል። ከዛ በመቀጠል የአብራሪነት ስልጠና ለመውሰድ እጩ መኮንን ሆነው የኢትዮጲያ አየር ኃይልን ቢቀላቀሉም፤ በአየር ኃይል የመዝናኛ ክፍል አባል በመሆን ከቴአትር ጋር ያላቸውን ቁርኝት አስቀጥለዋል።አርቲስት ደበበ የአየር ኃይል ትምህርታቸውን አቋርጠው በፖስታ ቤት ሥራ ተቀጥረውም ሰርተዋል። በአየር ኃይል ያቁረጡት ትምሕርት ሊያሳሥራቸው ስለሚችልም ወደ ደብረብርሃን አቅንተው የመምህርነት ስልጠና መከታተል ጀመሩ።በወቅቱ የማስልጠኛው ተማሪዎቹ ተቃውሞ በማስነሳታቸው አርቲስት ደበበም የዚሁ ተቃውሞ አባል ስለነበሩ፤ ለቅጣት ተዳርገው የፖለቲካ እስረኛ ሆነው ጎሬ ተላኩ።እስር የአርቲስቱን ሕልም አሁንም አልጋረደውም፤ ከእስር እንደተፈቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፐርፎርሚንግ አርትስ መማር ጀመሩ። የሀገር ውስጡን ትምህርታቸውንም አጠናቀው እ.አ.አ በ1965 ደግሞ ወደ ሃንጋሪ በማቅናት የቴአትር ጥበብን ከውጭ ሀገርም ቀነሱ። በሃንጋሪ ቆይታቸው ካገኙት ትምህርት በላይ የሃገራቸውን ልጆች እነ ተስፋዬ አውላቸው፣ ጌታቸው ደባልቄ፣ አስካለ አመነሸዋ እና ሌሎች ቀደምት ሙያተኞችን በማግኘታቸው ብዙ እውቀት መቅሰማቸውን ይናገራሉ። ደራሲ፤ ተርጓሚ፤ አዘጋጅ፤ ተዋናይ፤ መድረክ መሪና ሁለገብ አርቲስት ደበበ እሸቱ የቴአትርን ሥራ በቀድሞው ክሬቲቭ አርት ሴንተር ባሁኑ ባህል ማዕከል በይፋ ከጀመሩ ወዲህ ለኢትዮጲያ ኪነ ጥበብ በርካታ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ተሳትፏቸውም ከፍ ያለ ነው።አርቲስት ደበበ እናት ዓለም ጠኑ፣ የአዛውንቶች ክበብ፣ ኪንግ ሊር፣ ዋናው ተቆጣጣሪ፣ ዳንዴው ጨቡዴ፣ ያላቻ ጋብቻ፣ ናትናኤል ጠቢቡ፣ የቬኒሱ ነጋዴ፣ የከርሞ ሰው ከተወኑባቸው ቴአትሮች መካከል የሚጠቀሱ ሲሆን፤ 28 ተውኔቶችን አዘጋጅተው ለዕይታ አቅርበዋል።በእንግሊዘኛ ከሠራቸው ፊልሞች መካከልም ‘ሻፍት ኢን አፍሪካ’ 'ዘ ሴይለር ፍሮም ጂብራልታር'፣ 'ጉማ'፣ 'ዘ አፍሪካን ስፓይ'፣ 'ዜልዳ'፣ 'ዘ ግሬቭ ዲገር' እና 'ዘ ግሬት ሪቤሊየን ' ይጠቀሳሉ።በስነፅሁፍ ዘርፍም ከተዋናይ ሀሁ፤ የባሩድ በርሜል፤ድብልቅልቅ የመድረክ ተውኔት፣ ያልታመመው በሽተኛ፣ የደም እንባንና ሌሎችንም ሥራዎች ወደ አማረኛ ተርጉመዋል።አርቲስት ደበበ እሸቱ የአፍሪካ መድረክ ባለሙያዎች ማህበር መሥራች ፣የዓለም ኮንቴምፖራሪ ቴአትር ኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባል፤ የዓለም አቀፍ ቴአትር ኢንስቲቲዩት የአፍሪካ አስተባባሪና የኢትዮጵያ ተጠሪ፤በብሔራዊ ቴያትር የፕሮግራምና ፕሮዳክሽን ኃላፊ፤በሀገር ፍቅር ቴአትር የኪነጥበብ አገልግሎትኃላፊና፣በራስ ቴአትር ዋና ሥራ አስኪያጅነት፣ በአትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በርካታ ማህበራዊ፣ የልማትና እርዳታ አገልግሎቶችን ላይ አስተባባሪ፣ የሰላምና እርቅ ኮሚቴ አባል፣ የጌርጌሴኖን የአዕምሮ ህሙማን ማዕከል አምባሳደር፣ በኩላሊት ሞት ይብቃ አምባሳደር በመሆን አገልግለዋል። አርቲስት ደበበ እሸቱ ለአፍሪካ ቴአትር ባደረጉት አስተዋጽኦ የዚምባብዌን ማላካይት አዋርድ ተሸልመዋል፣ ጣይቱ ኢንተርቴንመንት በዋሽንግተን ዲሲ በቴአትር ዘርፍ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ አድርጓቸዋል። በአትላንታ ጂኦርጂያ የከተማው ምክር ቤት ለዓለም ቴአትር ባደረጉት አስተዋጽኦ ኖቬምበር 24ን የደበበ እሸቱ ቀን በሚል ሰይሞላቸዋል።
የኢትዮጵያ ባህል ሚኒስትርም ለኢትዮጵያ ፊልም እድገት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ሸልሟቸዋል። በጉማ አዋርድም የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ሆነዋል። እ.አ.አ በ2015 በቫንኮቨር ዓለምአቀፍ ፊልም ፌስቲቫልም በምርጥ መሪ ተዋናይ ዘርፍ ተሸላሚ ሆነዋል። በ2015 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሀገራቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ አበርክቶላቸዋል።አርቲስት ደበበ እሸቱ ከባለቤታቸው ወ/ሮ አልማዝ ደጀኔ ጋር በመሰረቱት የትዳር ሕይወታቸውም 4 ልጆችን አፍርተዋል።

በሰሜን ኮሪያ ዋና ከተማ ፒዮንግያንግ ግንባታው በተጀመረበት ዓመታት ከዓለማችን አስር ግዙፍ ህንጻዎች መካከል ተመድቦ የነበረ ትልቅና በመስታወት የተለበጠ ባለሦስት ማዕዘን ሕንጻ ከርቀት ቆሞ ይታያል።
ይህ በመሐል ከተማዋ  የሚገኘውና በተለይ በምሽት ለከተማዋ ትልቅ ድምቀት የሚሰጠው አስገራሚ ዲዛይን ያለው ግዙፍ ሕንጻ፤ በላዩ ላይ በተገጠሙት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኤል ኢ ዲ መብራቶች አማካኝነት የተለያዩ ሙዚቃዎችን  የርችት ምስሎችንና የሀገሪቱ ቴሌቪዥን መልእዕክቶችን በግዙፍ ስክሪኑ ያሳያል።
ርግዮንግ ሆቴል በመባል የሚታወቀው ይህ የርግያንግ ባለ 105 ፎቅ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ ለመገንባት ዓመታትን የወሰደ ሲሆን 1.5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ፈጅቷል።
ከውጭ ሲታይ የሚያስገርመው ሕንጻ በውስጡ 3 ሺህ ያህል የሆቴል ክፍሎችን እንዲይዝ ተደርጎ የተሰራ ሲሆን በዓይነታቸው ለየት ያሉና የፒዮንግያንግ ከተማን ከያቅጣጫው የሚያሳዩ አምስት ተሽከርካሪ ሬስቶራንቶችንም አካትቶ የያዘ ነበር ።
የሆቴሉ ግንባታ የተጀመረው በ1987 ሲሆን ስራው ለረጅም ጊዜያት ሲጓተት ከቆየ በኋላ፣ የሶቪየት ህብረትን መውደቅ ተከትሎ በተዳከመው የሰሜን ኮሪያ ኤኮኖሚ ምክንያት በኋላም በተለያዩ ማዕቀቦች በተፈጠረው የኤኮኖሚ ቀውስ በ1992 ሙሉ ለሙሉ ሳይጠናቀቅ ባለበት እንዲቆም ተደረገ ።
በዚህ መልኩ ዓመታት ከቆየ በኋላ በአንድ የግብፅ ኮንስትራክሽን ካምፓኒ አማካኝነት የህንጻው የውጭ ክፍል በመስታወት እንዲሸፈን ተደርጎ የተሻለ ገፅታ ተላበሰ።
ሆኖም በተለይ የውስጠኛው ክፍል ባለማለቁ ምክንያት አገልግሎት ሊሰጥ ስላልቻለ፣ የህንጻው ውስጠኛ ክፍል እየተጎዳ በተለይ እንደመወጣጫ ሊፍት ያሉ ብዙ ብር የወጣባቸው እቃዎች ከጥቅም ውጭ መሆን ጀምረዋል።
የሰሜን ኮሪያ መንግስት ከአንድ ቢሊየን ብር ወጭ ወጥቶበት ሊጠናቀቅ ያልቻለውን ይህን ግዙፍ ህንጻ በተመለከተ በ2012 ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ሲል ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም፤ እስከ አሁን እውን ሳይሆን ዓመታትን አስቆጥሯል።
እንደውም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ  ይህ 3 ሺህ ክፍሎችን እንዲይዝ ተደርጎ የተሰራው ሆቴል ወደ ትልቅ ስክሪንነት ተለውጧል ።
ታላቁ የርግያንግ ሆቴል ላይ ከ1 መቶ ሺህ በላይ የኤል ኢ ዲ መብራቶችን በመግጠም የተለያዩ ዲጂታል መልእክቶች ይተላለፉበታል ።
ከጥቂት ጊዜያት በፊት አንድ የጀርመን የሆቴል ድርጅት ግንባታውን አጠናቆ ወደ ሥራ ለማስገባት አስቦ የነበረ ቢሆንም፤ ሳይጠናቀቅ ዓመታት የፈጀውን ሆቴል ጨርሶ ወደ ሆቴልነት ለመለወጥ እስካሁን ከወጣበት ወጪ ሌላ 1 ቢሊየን ዶላር እንደሚፈጅ በመታወቁ ሀሳቡን ሰርዟል።
ከውጭ ሲታይ አስገራሚ ዲዛይን ያለው ይህ ከ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የፈጀ የሰሜን ኮሪያ ያላለቀ ሆቴል ውስጡ ባዶ ሆኖ ግዙፍ የቪዲዮ ስክሪን ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።

አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ በሴቶች 10 ሺህ ሜትር ሦስት የወርቅ ሜዳልያዎችን በማምጣት የሚስተካከላት የለም፡፡
በዚህ ርቀት በመድረኩ የኢትዮጵያን ያህል የወርቅ ሜዳልያ ያለው ሀገርም የለም፡፡ ኢትዮጵያ በእንስት አትሌቶቿ 9 የወርቅ ሜዳልያ ያላት ሲሆን ኬንያ በ4 ሜዳልያዎች 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
ብርሀኔ አደሬ በ2003 የፓሪስ ዓለም ሻምፒዮና 10 ሺህ ሜትሩን ያጠናቀቀችበት 30 ደቂቃ 04.18 ሰከንድ አሁንም ድረስ የሻምፒዮናው ክብረ ወሰን ሆኖ የተቀመጠ ነው፡፡ በዓለም ሻምፒናው የርቀቱ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ምርጥ ሰዓት ባለቤቶችም ብርሀኔ አደሬ፣ ለተሰንበት ግደይ እና አልማዝ አያና ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በበርካታ መመዘኛዎች ፍጹም የበላይ በመሆነችበት የሴቶች 10 ሺህ ሜትር ፍጻሜ በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ለሌላ ክብር በጀግኖች ልጆቿ ትፎካካራለች፡፡
በቶኪዮ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የዓለም አትሌቲከስ ሻምፒዮና ዛሬ በይፋ ሲጀመር የዓለም አትሌቲክስ አፍቃሪ በጉጉት የሚጠብቀው የሴቶች 10 ሺህ ሜትር ፍጻሜ ቀን 9 ሰዓት ከ30 ላይ ይካሄዳል፡፡
ኢትዮጵያ በመጀመርያው ቀን የመጀመርያ ሜዳልያዋን ታገኝበታለች ተብሎ በሚጠበቀው ውድድር 27 አትሌቶች ተፋጠዋል፡፡ በውድድሩ ኢትዮጵያ በብቸኝት በአራት አትሌቶች ትወከላለች፡፡
የ2023 የቡዳፔስ ዓለም ሻምፒዮና የርቀቱ አሸናፊ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በቀጥታ የመሳተፍ ዕድል ባገኘችበት መድረክ ጽጌ ገ/ሰላማ፣ እጅጋየሁ ታዬ እና ፎተይን ተስፋዬ ሌሎች ለአሸናፊነት የሚፎካከሩ አትሌቶች ናቸው፡፡
ከሚሳተፉት 27 አትሌቶች ርቀቱን ከ30 ደቂቃ በታች መግባት የቻሉ አምስት አትሌቶች ያሉበት መሆኑ የውድድሩን ፉክክር በእጅጉ ፈታኝ ያደርገዋል፡፡ ከአምስቱ አትሌቶች ደግሞ ከኬንያዊቷ ቢያትሪስ ቺቤት ውጭ አራቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡
አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በላፉት 3 የዓለም ሻምፒዮና መድረኮች ሁለት የወርቅ አንድ የብር እና አንድ የነሃስ ሜዳልያዎች ያሏት ሲሆን ዛሬ ሦስተኛውን ወርቅ ለማምጣት በምትወዳደርበት መድረክ ከኬንያዊቷ አትሌት ቢያትሪስ ቺቤት ጋር ትልቅ ትንቅንቅ እንደምታደርግ ይጠበቃል፡፡
የቡዳፔስት ዓለም ሻምፒዮና የነሃስ ሜዳልያ ባለቤቷ እጅጋየሁ ታዬ፣ ጽጌ ገ/ሰላማ እና ፎተይን ተስፋዬ በቶኪዮ ለመድመቅ የተዘጋጁ ናቸው፡፡
የፓሪስ ኦሎምፒክ የ5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ባለቤቷ ቢያትሪስ ቺቤት የ10 ሺህ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰንን በእጇ ከማስገባቷ በተጨማሪ ምርጥ ወቅታዊ ብቃት ላይ መገኘቷ ከጉዳፍ ጋር የምታደርገውን ፉክክር ተጠባቂም እንዲሆን አድርጎታል፡፡
10 ሺህ ሜትርን ከ29 ደቂቃ በታች በመግባት ብቸኛዋ አትሌት ቺቤት ከቪቪያን ቺሪዮት በኋላ ኬንያ ለ10 ዓመት ያጣችውን ወርቅ ለማሳካት ትወዳደራለች፡፡ ሌላኛዋ ኬንያዊት አትሌት አግነስ ንጌቲች እና ጃን ችፕንጌቲች በትልቁ የሚጠበቁ አትሌቶች ናቸው፡፡
አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በ2005 እና በ2007 ጥሩነሽ ዲባባ በተከታታይ ያሸነፈችበትን ገድል ለመድገም በጃፓን ብሔራዊ ስቴዲም ውድድሯን የምታደርግም ይሆናል፡፡
ሦስቱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ትልቅ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ በሚጠበቀው የ10 ሺህ ሜትር ፍጻሜ ርብቃ ቺፕቴጌይ፣ ሳራ ቸላንጋት እና ጆይ ቼፕቶይክ ዩጋንዳን የሚወክሉ አትሌቶች ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ. ግንቦት7 ቀን 1998 አሜሪካን ካንሳስ ውስጥ የተወለደው አሜሪካዊው ዝነኛ ዩቲዩበር ጂሚ ዶናልድሰን (ሚስተር ቢስት) የመጀመሪያ የዩቲዩብ ቪዲዮውን የሰራው የ13 ዓመት ታዳጊ እያለ ነበር።
ሆኖም የእውቅናው ማማ ላይ ለመውጣት በርካታ ዓመታትን ፈጅቶበታል። ጂሚ ዶናልድሰን አሁን ላይ ከዩቲዩበርነቱ ባልተናነሰ በበጎ ምግባሩ የሚጠቀስ የ27 ዓመት ወጣት ነው።
በጤና፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በማኀበራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ላይ የሚሰራው ሚስተር ቢስት በስሙ የሚጠራ የበጎ አድራጎት ተቋም አማካኝነት እስካሁን ከ50 ሚሊየን ዶላር የሚበልጥ ገንዘብ  ወጪ በማድረግ የተለያዩ መልካም ተግባራትን አከናውኗል።
ኮምፒውተሮችን እና የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ያሟሉ ትምህርት ቤቶች፣  ለወጣቶች የሚሆኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ ሆስፒታል እና የጤና ተቋማትን አስገንብቷል።
በአሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ለሚገኙ የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው ሰዎች በሚሊዮኖች ዶላር በማውጣት የምግብ እርዳታ አድርጓል።
የተቀናጡ ግዙፍ ቪላዎችን ከመግዛት እና ሚሊዮን ዶላሮች የሚያወጡ አስር መኪኖችን ከመቀያየር ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችሉ የዩቲዩብ ቪዲዮዎችን መስራት እንደሚመርጥ የሚናገረው ዶናልድሰን ማኀበራዊ ሚዲያን ለበጎ ተግባር ለማዋል እና የደግነት እጁን ለመዘርጋት ውቅያኖስ አያግደውም ይባልለታል።
በደቡብ አሜሪካ፣ በኤዥያ፣፡ በአፍሪካ እና በተለያዩ አህጉራት የልግስና እጁ ደርሷል። በዚህ የበጎ አድራጎት ሥራው በአፍሪካ በተለያዩ ሀገራት ራሱ በአካል እየተገኘ ለመጠጥ የሚሆን የውሃ ጉድጓድ  አስቆፍሯል።
በዚህም በካሜሩን፣ በዚምባቡዌ፣ ኡጋንዳ እና ኬንያ ለሚገኙ የገጠር ከተሞች ለዓመታት የሚያገለግሉ እና ግማሽ ሚሊዮን ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አንድ መቶ የውሃ ጉድጓዶችን አስቆፍሮ ለአካባቢው ነዋሪዎች አስረክቧል።
በአንድ የኬንያ የገጠር መንደር በተገኘበት ወቅት ለደህንነት አስጊ የሆነ አሮጌ የእንጨት ድልድይን አስፈርሶ ዘመናዊ ድልድይ አስገንብቷል።
በኤልሳልቫዶር፣ ጃማይካ እና አርጀንቲና ውስጥ ለሚገኙ ችግረኞች አንድ መቶ ቤቶችን ገንብቶ የቤት እቃዎችን አሟልቶ ሰጥቷል።
በአሜሪካ እና በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ሶስት ሺ የአካል ጉዳተኞች ሰው ሰራሽ እግር እንዲያገኙ አድርጓል፤ በደቡብ አፍሪካም ወላጆቻቸውን ላጡ ልጆች ቤት ሰርቶ ሰጥቷል።
ይህ ብቻም አይደለም በኤዥያ በህንድ በዓይን በሽታ እይታቸውን ላጡ አንድ ሺህ ሰዎች ሙሉ የዓይን ቀዶ ሕክምና ወጪ በማድረግ እይታቸው እንዲመለስ ረድቷል።
በፊሊፒንስ የመስማት ችግር ለነበረባቸው ሰዎች ቀዶ ሕክምና ወጪ በማድረግ ጤናቸው እንዲመለስ አድርጓል።
በአሜሪካ በምግብ ራሳቸውን ላልቻሉ እና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች የአስቸኳይ ምግብ እርዳታ ሰጥቷል።  በተለያዩ የአሜሪካ ከተማ ለሚኖሩ ትምህርት ቤቶች ድጋፍ አድርጓል።
የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተ አብረውት ከሚሰሩ ተቋማት ጋር በመሆን በተለያዩ ሀገራት 23 ሚሊየን ችግኞችን እንዲተከሉ ሰርቷል።
በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የባህር ዳርቻዎችን በማፅዳት 33 ሚሊየን ፓውንድ የሚመዝኑ የተጣሉ ፕላስቲኮችንና ቆሻሻዎችን እነዲጸዱም ረድቷል።
እድሜውን በሙሉ በዚህ መሰል የበጎ አድራጎት መቀጠል እንደሚፈልግ የሚናገረው ሚስተር ቢስት በዩቱዩብ ሰብስክራይበር ብዛት ተወዳዳሪ በሌለው ቻናሉ እ.አ.አ. በ2024 ከዩቲዩብ ብቻ 85 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ችሏል።
የሀብቱ መጠንም አንድ ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የቅርብ ጊዜ የፎርብስ ዘገባ አመላክቷል።

ብሪክስ እና የአፍሪካ አህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጠና (AfCFTA) እርስ በእርስ የሚፎካከሩ ሳይሆኑ፣ አፍሪካን ወደ አዲስ የኢኮኖሚ ጥንካሬ ዘመን ሊያመጡ የሚችሉ አጋዥ ኃይሎች ናቸው።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነቷን እንዴት ትጠቀማለች የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው። ይህ አጋርነት የምዕራባውያን ጥገኝነትን በብሪክስ ከመተካት ይልቅ፣ የአፍሪካ ኢንዱስትሪዎችን የሚያጠናክር፣ የመሰረተ ልማቶችን የሚያሻሽል እና ቀጣናዊ ንግድን የሚያቀላጥፍ መሆን አለበት።
የኢትዮጵያ ወደ ብሪክስ መግባት፣ ከ126 ሚሊዮን በላይ ህዝብ፣ እያደገ ያለ የማምረቻ ኢንዱስትሪ እና እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ (GERD) ያሉ ትልልቅ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች አንጻር፣ ወቅታዊ ነው። ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ገበያዎች መካከል እንደ ወሳኝ ማገናኛ ድልድይ ሆናም እየሰራች ነው።
የብሪክስ አባላት በተለይም ቻይና፣ ህንድ እና ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ቀድሞውንም ጠንካራ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ግንኙነት አላቸው።
ይህ አዲስ አባልነት የቀጣናዊ ውህደትን ያበረታታል። ለምሳሌ፣ የብሪክስ ድጋፍ ያላቸው በኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ መስክ ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች፣ እንደ የጅቡቲ ኮሪደር እና በድሬዳዋና ሀዋሳ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የአፍሪካ አህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጠናን (AfCFTA) የመገናኛ እና የድንበር ተሻጋሪ ንግድ ማሻሻያ ግቦችን ያሳድጋሉ።
የአፍሪካ አህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጠና AfCFTA የአፍሪካን የእርስ በእርስ ንግድን በ2030 ከ50 በመቶ በላይ ሊያሳድግ ይችላል።
ይህንን ለማሳካት ግን የንግድ ስምምነቶች ብቻ በቂ አይደሉም፤ ከፍተኛ የካፒታል፣ የቴክኖሎጂ፣ የመሰረተ ልማት እና የተቀናጀ የፖሊሲ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል።
እንደ ኢንፎብሪክስ ዶት ኦርግ መረጃ የብሪክስ ቡድን በተለይም እንደ አዲሱ የልማት ባንክ (NDB) ባሉ ተቋማት አማካኝነት ከአፍሪካ ውጭ ባሉ የገንዘብ ተቋማት ከሚሰጡ ጥብቅ የብድር ሁኔታዎች ነፃ የሆነ አማራጭ የገንዘብ ምንጭ ይሰጣል።
እንደ ብሪክስ አባል ኢትዮጵያ አሁን ወደ አዲሱ የልማት ባንክ (NDB) የላቀ ተደራሽነት በማግኘት፣ ከአፍሪካ አህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጣና AfCFTA ጋር የሚጣጣሙ እና ለጎረቤት አገራትም አዎንታዊ ተጽእኖ የሚፈጥሩ ፕሮጀክቶችን በገንዘብ መደገፍ ትችላለች።
በተጨማሪም የብሪክስ አባልነት በአፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ለትብብር ትልቅ እድል ይሰጣል። የብሪክስ አባላት የሆኑት ህንድ እና ቻይና በዲጂታል ቴክኖሎጂ እና በሰፊ ደረጃ ሊተገበሩ በሚችሉ መፍትሄዎች ሰፊ እውቀት አላቸው። የእነሱ ተሳትፎ አህጉር አቀፍ የዲጂታል ገበያ በመፍጠር፣ መሰናክሎችን በማስወገድ እና አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን (SMEs) ወደ ቀጣናዊ የዋጋ ሰንሰለቶች ለማዋሃድ ጠቃሚ ነው።

ኖኪያ የሚባል ስም በዓለም ላይ እንዲታወቅ የሆነበት አጋጣሚ አጭር ቢሆንም ረጅም ዘመን ውስጥ የጥንካሬ እና የቴክኖሎጂ ሥም መሆኑ ግን አያጠራጥርም።
በዚሁ ልክ ደግሞ በርቶ መጥፋት፣ ነገን ሳያሳቡ ዛሬ ላይ መምከን፣ ቆሞ ቀርነት ወይም ከዘመን ጋር አለመዘመን ሲነሳ በተለይ ለቢዝነስ ሰዎች በማስተማሪያነት የሚነሳም ሥምም ነው ኖኪያ።
ከ160 ዓመታት በፊት በፊንላንድ ታምፒሪ በምትባል ከተማ ሲመሰረት ዋና መሰረቱ ወረቀት እና የወረቀት ውጤቶች ላይ በማተኮር ነበር። በእርግጥ በዚህ ወቅት ኖኪያ እጅግ ፈጣን ተቀባይነት በማግኘቱ ፊቱን ወደሌሎች ፋብሪካዎች ሲያዞር ብዙም ጊዜ አልወሰደም።
ኖኪያ የኢንደስትሪውን ዘርፍ በማስፋት አዲስ በከፈታቸው ፋብሪካዎችም የፕላስቲክ ጫማዎችንና የኤሌክትሪክ ገመዶችን (ኬብሎችን) በማምረት ቀስ በቀስ ወደኤሌክትሮኒክስ ኢንደስትሪው ዓለም  ተሸጋገረ።
በዚህም የኖኪያ ምርቶች የሆኑ የጥቁርና ነጭ ቴሌቪዥኖች በፊንላንድ ገበያዎች ብቅ ብቅ ማለት ሲጀመሩ በዚህ ሁኔታ  ዓመታትን በስኬት እየተሻገረ የቀጠለው ኖኪያ በተለያዩ ምርቶቹ ድንበር ተሻጋሪ እውቅና እያገኘ ሄደ።
ጊዜው በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ በእጅ የሚያዙ ስልኮች የዓለምን ህዝብ ትኩረት የሳቡበት ወቅት ነበር። እና በዚህ ወቅት ከመቶ ዓመታት በፊት ከወረቀት ተነስቶ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን በማምረት ራሱን ግዙፍ ኩባንያ ማድረግ የቻለው ኖኪያ ሞባይል ስልኮችን ወደማምረት ትልቅ ደረጃ ተሸጋገረ።
በኩባንያው የመቶ ዓመታት ታሪክ ውስጥም ከስር መሰረቱ የለወጠውና በዓለም ደረጃ ዝነኛ ያደረገው የኢንደስትሪ እመርታ ይሄው ወደ ሞባይል ስልኮች ማመረት የተሸጋገረበት ጊዜ ነው።
ኖኪያ ሙሉ አቅሙንና የተመራማሪዎቹን እምቅ እውቀት ተጠቅሞ ቀላል፣ ጠንካራና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ያካተቱ በወቅቱ ዓለምን ያስደንቁ የነበሩ አዳዲስ ሞዴል የሞባይል ስልኮችን ማምረት ጀመረ።
የጽሑፍ መልዕክቶችን መላክ የሚያስችሉ እንዲሁም “ስኔክ” የተሰኘውን በወቅቱ ተወዳጅ የነበረ የሞባይል ጌም ያካተቱ የኖኪያ ስልኮች ተቀባይነት ከሚታሰበው በላይ ሆነ።
በጥቂት ዓመታት ውስጥም የኖኪያ የእጅ ስልኮች በሚሊዮኖች እጅ የሚያዙ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ኖኪያ የምድራችን ግዙፍ፣ ታዋቂ እና ተወዳጅ ኩባንያ መሆን ቻለ።
በተለይ ኖኪያ በአውሮፓውያኑ 2003 ላይ ወደገበያ ያቀረበው 1100 ሞዴል የሞባይል ስልክ የዓለምን የሞባይል ስልክ ገበያ ተቆጣጠረው። እስከዛሬም ድረስ በምድራችን ከተሸጡ የሞባይል ስልኮች የኖኪያ 1100 ያህል ሰፊ ተቀባይነት ስልክ ያለው የለም።
እስካሁን ሪከርዱን የያዘው ይህ ስልክ 255 ሚሊዮን ሰዎች ገዝተውት ነበር። ከዚያም ከሁለት ዓመት በኋላ በ2005 ሌላውን 1110 የተባለ ስልክ ለገበያ አቀረበ። ይህም አዲስ ምርት 247 ሚሊዮን ስልኮችን መሸጥ ቻለ። ይህኛውም ስልክ እስከዛሬ በብዛት መሸጥ ከቻሉ የሞባይል ስልኮች ሁለተኛ በመሆን እየመራ የሚገኝ ስልክ ነው። በዓለም ዙሪያ ኖኪያ ተወዳዳሪ የሌለው የሞባይል ስልክ አምራች መሆኑን ዳግም አስመሰከረ ።
ኖኪያ በዚህ በስኬት ላይ ስኬት እያስመዘገበ በሚሄድበት ወቅት ተወዳዳሪ የሆኑ የሞባይል ስልክ አምራች ኩባንያዎች የተሻለ ቴክኖሎጂ እና የአመራረት ዘዴን ይዘው በመቅረብ ኖኪያ የተቆጣጠረውን ገበያ ለመሻማት ምርምራቸውን ቀጠሉ።
በዚህ የምርምር ሥራ ውስጥ የነበረው አፕል ካምፓኒ አንደኛው ነበር።  አፕል በዚህ ለዓመታት በምስጢር ይዞ ሲያከናውን የነበረውን የሞባይል ስልኮችን ታሪክ ከስር መሰረቱ የቀየረውን ትላልቅ መስታወት (wide screen) ያላቸው ስማርት ስልኮችን ይፋ አደረገ።
እነዚህ ከኢንተርኔት ጋር መገናኘት የሚችሉ ስልኮች ወደገበያው መምጣት የሰው ፍላጎት ከኖኪያ መሰል ስልኮች ይልቅ በአዳዲሶቹ ላይ በመሆኑ ኖኪያም ገበያው መቀዛቀዝ ጀመረ።
ለዓመታት ብዙ ውስብስብ ባልሆኑ የ "ጠቅ ጠቅ " ስልኮች የዓለምን ገበያ ተቆጣጥሮ የነበረው ኖኪያ የቴክኖሎጂውን መዘመን ቶሎ መቀበል አልችል አለ። እዚህ ላይ በወቅቱ የነበሩ የኖኪያ አመራሮች በኖኪያ ስኬት መኩራራት እና ጊዜን በድግስ ላይ ማሳለፍ መምረጣቸው አንዱ ምክንያት ተድርጎ ይነሳል። የኖኪያ ስኬት በዓለም ላይ የናኘ ስለነበር ኖኪያን መገዳደር የሚችል ተቋም መፍጠር የሚታሰብ አይደልም ይልቁንም ትንንሽ የኖኪያ አይነት ድርጅቶች ቢመጡ እንደሁ እንጂ የሚሉ ነገን መተንበይ ያልቻሉ ሃሳቦችም ገዝፈው ኖኪያን ወረውታል። ኖኪያ የሚታደስ አለመሆኑ የገባቸው እና ቆሞ ቀርነቱን የተረዱ ተመራማሪዎች ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ምስጢራዊ ግንኙነት ጀምረው ሌላ የነገውን ኖኪያ ለመፍጠር ሥራ ላይ ናቸው። ኖኪያም ራሱን ከዘመንና ከቴክኖሎጂ ጋር ከማዘመን ይልቅ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቶባቸው በነበሩት መደበኛ ስልኮች ላይ  አተኩሮ መቆየትን መረጠ።
ኖኪያ የተለመዱትን ስልኮች እየሸጠ በነበረባቸው ዓመታት ያገኝ የነበረው ገቢ በቢሊዮን የሚቆጠር ነበር። አዳዲስ ስልኮች ይዘው ወደገበያው የመጡ ድርጅቶች ሊወዳደሩት እንደማይችሉ የተሳሳተበት ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ኖኪያ በገበያው ውስጥ ያለው ድርሻ ነው። የአዳዲሶቹ ስማርት ስልኮች ወደገበያ ከመጡም በኋላ ቢሆን የዓለም 50 በመቶ የሞባይል ስልኮች ገበያ በኖኪያ እጅ ስር ነበር። በ2009 ኖኪያ ከተለመዱት የስልክ ምርቶቹ 4 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘት ችሎ ነበር።
ሆኖም የስማርት ስልኮች በህዝብ ዘንድ ተወዳጅነታቸው እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ኖኪያ ራሱን ከቴክኖሎጂው ጋር  ባለማዘመኑ የካምፓኒው አስደንጋጭ የቁልቁለት ጉዞ በ2010 ላይ ጀመረ ።
በዓለም ደረጃ እጅግ ተወዳጅና ተመራጭ የነበረው ኖኪያ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ይዘው ወደገበያው የተቀላቀሉትን አፕልን እና ሳምሰንግን መወዳደር አቃተው።
በዚህም ምክንያት በስድስት ዓመታት ውስጥ ታላቁ ኖኪያ 90 በመቶ የሚሆነው የስልክ ገበያውን በተወዳዳሪዎች ተነጠቀ።
የወረቀት ምርቶችን፣ የፕላስቲክ ምርቶችን፣ የኤሌክትሪክ ገመዶችን (ኬብሎችንና) ቴሌቪዥኖችን በማምረት ጀምሮ በሞባይል ስልኮች የዓለምን ገበያ ለዓመታት ይዞ የነበረው ኖኪያ ራሱን ማዘመን ባለመቻሉ ከሞባይል ስልክ ዓለም ራሱን ማሰናበት ግድ ሆነበት።
በ2014 ላይ ኖኪያ ካምፓኒ ሙሉ በሙሉ ከስሮ ለማይክሮሶፍት ኩባንያ ተሸጠ። ዛሬ ላይ የፊንላንዱ ኖኪያ ኔትወርክ ዝርጋታ ላይና የ5ጂ ቴሌኮም አገልግሎቶችን በማስፋፋት ስራ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል።
ኖኪያ በእርግጥ በድንገት ቢሆንም ታዋቂነቱን ያመጣው በሂደት ይህን ተጽዕኖ ፈጣሪነቱ በዓለም ላይ ጠብቆ ለመቆየት ብዙ ሰርቷል። በሰው ልጅ የስልጣኔ ዘመን ውስጥ ስሙን በጉልህ ጽፏል። የገበያ ድርሻውም ቢሆን ቀላል ባለመሆኑ አዲስ መጥተው ሥራውን የበለጡት ድርጅቶች እንኳ ዓመታትን ፈጅቶባቸዋል።
ኖኪያ በዓመታት ውስጥ የገነባውን ዝና ለማጣት ግን ጥቂት ዓመታት ብቻ ናቸው የፈለገው። ዛሬ ላይ ኖኪያ ከገነባው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋምነቱ ይልቅ አንድ ተቋም እንዴት በፍጥነት ካለበት ደረጃ ሊወርድ እንደሚችል ማስተማሪያነቱ ይገዝፋል። በእርግጥ ለብዙዎቹ የቴክኖሎጂ ተቋማት መፈጠር ምክንያት መሆኑ አያጠያይቅም።
እዚህ ላይ ግን አሁን ላይ ፈጣን እና ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ውስጥ ራስን ከዘመኑ ጋር ማራመድ አለመቻል ራስን የማጥፋት ያህል ከባድ ውሳኔ እንደመወሰን የሚቆጠር ነው። ኖኪያም ይህን ዕጣ ፈንታ በራሱ ላይ በመወሰን በዓመታት የገነባውን ተቋም ከገበያ ውጭ ለማድረግ 6 ዓመታት ብቻ ነው ተንገዳግዶ መቆየት የቻለው።
ቆሞ ቀርነት በትክክልም የጎዳው ተቋም ቢኖር ኖኪያ ነው ለማለት ጥቂት ሰከንዶች እንኳ ማሰላሰል የሚፈልግ አይመስልም።  ዛሬ ከግለሰብ እስከ ማሕበረሰብ ከተቋም እስከ ሀገር በኖሩበት ዓለም በሚያውቁት መንገድ ብቻ መጓዝ የሚያስከፍለውን ዋጋ ከኖኪያ የሚማሩበት ታሪክ ሆኖ ተሰንዷል።

ኪን ኢትዮጵያ የባህል እና የጥበብ ቡድን በሩሲያ ሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ለሩሲያ ታዳሚያን ሕብረ ብሔራዊነትን የሚያንፀባርቁ የተለያዩ የባህል እና የኪነ-ጥበብ ሥራዎችን አቅርቧል።
በመድረኩ የታደሙ ሩሲያዊያን የኢትዮጵያን ባህል፣ ጥበብ እና አኗኗር የሚያሳዩ ዝግጅቶች ቀልብ የሚስቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያውያንን የሙዚቃ ምቶች በመስማታቸው እና ቆንጆ የባህል አለባሳትን በማየታቸውም መደሰታቸውን ገልጸዋል።
የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲ፤ ዝግጅቱ የታለመለትን ግብ መምታቱን አስታውቀዋል።
ኪን-ኢትዮጵያ ዝግጅቱን ያቀረበበት መንገድ የታዳሚውን ትኩረት የሳበ እንደነበር አንስተዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክቶሬት ጀነራል የሆኑት አምባሳደር ነብዩ ተድላ በበኩላቸው፤ በመድረኩ የቀረበው ትዕይንት በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል ያለውን የባህል ትስስር ያጠናክራል ብለዋል።
በሩሲያ ሴንት ፒተስበርግ የቀረበው የኪን ኢትዮጵያ ዝግጅት ለቀጣይ የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች መደላድል የፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።
የሻኩራ ፕሮዳክሽን ሥራ አስኪያጅ ካሙዙ ካሳ የመድረክ ዝግጅቱ ኢትዮጵያን ያስተዋወቀ መሆኑን አስረድቷል።
ዝግጅቱ አንድነት የታየበት እና ሕዳሴ በተመረቀበት ማግስት የቀረበ በመሆኑ በእጅጉ እንዳስደሰተው ገልጿል።
በተጨማሪም የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲ ከሩሲያ ባህል ፌዴሬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ጃና አሌክሳቫ ጋር ተወያይተዋል።

ምጡቅ ሠው ሰራሽ አስተውሎት (AI )የዓለምን ኢኮኖሚ፣ ጂኦፖለቲካ እና ማኅበራዊ መስተጋብርን እየቀየረ ያለ ወሳኝ ኃይል ነው። ከዚህ ቀደም በዋነኛነት በሲልከን ቫሊ እና በምዕራባውያን የቴክኖሎጂ ግዙፍ ድርጅቶች ቁጥጥር ስር የነበረው የምጡቅ ሠው ሰራሽ አስተውሎት (AI ) ልማትና አስተዳደር፣ አሁን ላይ ብሪክስ ፕላስ በሚመራ አዲስ የቴክኖሎጂ ኃይል ፈተና እየገጠመው ነው። ይህ ዘርፉ ሀገራቱ የፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትብብራቸውን ማዕከል በማድረግ፣ የራሳቸውን የዲጂታል ሉዓላዊነት ለመፍጠር እና ለታዳጊ ሀገራት ተስማሚ የሆኑ የቴክኖሎጂ መፍትሄዎችን የማቅረብ ስልት እየተከተሉ ነው።
የብሪክስ ማስፋፋትና አዳዲስ አባላትን (ኢትዮጵያን ጨምሮ) በማካተቱ ሰፊ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ክብደት አግኝቷል። ከ2024 የካዛን ስብሰባ በኋላ ግን፣ ስብስቡ የፖለቲካ ፍላጎት ከማራመድ ባለፈ፣ "የብሪክስ ፕላስ  AI ትብብር ማዕቀፍ" በሚል ስልታዊ ተነሳሽነት ራሱን እንደ ቴክኖሎጂ ኃይል አቋቁሟል። ይህ ማዕቀፍ፣ በጋራ የምርምር ማዕከላት፣ በዲጂታል መሠረተ ልማት እና በጋራ የሥነ-ምግባር ደንቦች ላይ ያተኩራል።
ለዓመታት ታዳጊ ሀገራት በጎግል፣ አማዞን፣ ማይክሮሶፍት እና ሌሎች የምዕራባውያን ኩባንያዎች ላይ ጥገኛ ሆነው ቆይተዋል። ይህ ጥገኝነት የዳታ ሉዓላዊነት እና የሳይበር ደህንነት ስጋቶችን ከማስከተሉም በላይ፣ በምዕራባውያን አውድ ላይ ብቻ የተመሠረቱ AI ሞዴሎች በአካባቢው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ላይ ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል። ብሪክስ ፕላስ ግን የራሱን የ “የብሪክስ ፕላስ ዲጂታል ክላውድ ኮሪደር” በመገንባት፣ አባል ሀገራት የራሳቸውን የ AI ሞዴሎች ያለ የውጭ ጥገኝነት እንዲያዳብሩ እያገዘ ነው።
ከባህላዊ የሰሜን-ደቡብ የእርዳታና የልማት ግንኙነት በተለየ፣ የብሪክስ ፕላስ AI ትብብር በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ነው። ፕሮጀክቶቹ ከአንድ የቴክኖሎጂ የበላይ ሀገር ወደ ሌሎች የሚደረግ ዝውውር ሳይሆን፣ እያንዳንዱ አባል አገር የራሱን ልዩ እውቀትና ልምድ እንዲያበረክት በሚያስችል መንገድ የተቀረጹ ናቸው። ለምሳሌ ቻይና በጥልቅ ትምህርት፣ ሕንድ በዳታ ሳይንስና ሶፍትዌር፣ ሩሲያ በሮቦቲክስ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በግብርናው ዘርፍ የአካባቢ ተስማሚነት ያላቸውን የ AI መፍትሄዎች በመፍጠር አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።
ለአፍሪካ ሀገራት በተለይም ለኢትዮጵያ፣ የብሪክስ ፕላስ አባልነት ለAI ትብብር በር ከፍቷል። ይህ አባልነት በቴክኖሎጂ ዘርፍ ከውጭ የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ እና የእውቀት ልውውጥን ማመቻቸት ብቻ ሳይሆን፣ አፍሪካ የራሷን የዲጂታል የወደፊት እጣ ፈንታ እንድትቀርጽ ያስችላታል።
በብሪክስ ፕላስ ድጋፍ ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው የAI መድረክ የድርቅ ትንበያዎችን እና የመስኖ ካርታዎችን ለመስራት የሚያስችል ፕሮጀክት ለሀገሪቱ የምግብ ዋስትና ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ይህ ከአጠቃላይ የAI መፍትሄዎች በተለየ የአካባቢውን ችግር በቀጥታ ለመፍታት የሚረዳ ነው።
በትብብሩ ስር የሚካሄዱ የሙያተኞች ስልጠናዎች እና የእውቀት ሽግግሮች ኢትዮጵያ የራሷን የAI ባለሙያዎች ማፍራት እንድትችል ይረዳታል። ይህ ደግሞ በረጅም ጊዜ ውስጥ የቴክኖሎጂ ጥገኝነትን በእጅጉ ይቀንሳል።
የብሪክስ ፕላስ ዲጂታል መሠረተ ልማት ግንባታ፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት የጤና እና የትምህርት መረጃዎችን በውጭ ሰርቨሮች ላይ ሳያስተናግዱ፣ በሀገር ውስጥ ወይም በትብብሩ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲያከማቹ ያስችላቸዋል። ይህ የዳታ ደህንነትንና ሉዓላዊነትን ለመጠበቅ ወሳኝ ነው።
ብሪክስ ፕላስ በAI ትብብር ላይ እየገነባ ያለው አዲስ የዓለም ሥርዓት ከምዕራባውያን ሞዴሎች አማራጭን ብቻ ሳይሆን፣ የተለየ የሥነ-ምግባር ፍልስፍናም ይዞ ይመጣል። “የተዋሃደ የAI ሥነ-ምግባር ቻርተር” የፍትሃዊነት፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነት መርሆዎችን የሚያጎላ ቢሆንም፣ ከምዕራባውያን አገራት የሰብዓዊ መብት አተያይ እና የነፃነት ፍልስፍና ጋር ሊኖረው የሚችለው ልዩነት አሁንም ክትትል የሚሻ ጉዳይ ነው።
በአጠቃላይ፣ የብሪክስ ፕላስ AI ትብብር የዓለምን የቴክኖሎጂ ሥርዓት ዳግም እየቀረጸ ያለ አዲስ ምዕራፍ ነው። ይህ እንቅስቃሴ የሲልከን ቫሊ የበላይነት ማብቃቱን የሚያሳይ ግልጽ ምልክት ሲሆን፣ ታዳጊ ሀገራት የቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ የራሳቸውን እጣ ፈንታ የሚወስኑ ፈጣሪዎችና ተዋናዮች መሆናቸውን ያበስራል።

የአሜሪካው ሁቨር ግድብ የአሜሪካ ኢንጂነሪንግ ዕድገት እና የማድረግ አቅም ተምሳሌት ነው። ይህ ግድብ በአሪዞና እና በኔቫዳ ግዛቶች ወሰን አካባቢ በኮሎራዶ ወንዝ ላይ የተገነባ ግዙፍ የኮንክሪት ቅስት ግድብ ነው።
ግድቡ የሰው ልጅ በጥንካሬ እና በብልሃት ተፈጥሮን እንዴት በቁጥጥሩ ሥር ማዋል እንደሚችል ማረጋገጫ ምልክትም ተደርጎ ይወሰዳል።
በ1900ዎቹ መጀመሪያ ላይ፣ የኮሎራዶ ወንዝ በደቡብ ካሊፎርኒያ ውስጥ የእርሻ ቦታዎችን በጎርፍ ጠራርጎ በመውሰድ የአካባቢ ነዋሪዎች የሀዘን ምንጭ የነበረ ነው። በአካባቢው የእርሻ ሥራ ለማከናወን የሚተጉ አሜሪካውያን የኮሎራዶ ወንዝ ጥፋት እንዳይመጣ በመፅለይ ጭምር ነው። ምክንያቱም ባንድ ቅጽበት ኮሎራዶ ሁሉን ነገር ጠራርጎ የነበረውን እንዳልነበር በማድረግም ይታወቃል።
በሌላ በኩል ደግሞ ደረቃማ የሆኑት የደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ለመስኖ እና የሕዝቡን ብዛት ያማከለ አስተማማኝ የውኃ አቅርቦት በጣም ያስፈልግ ነበር። በረሃውን ለብቻው እየጋለበ የሚጓዘው ኮሎራዶ ሲሳይ መሆን ሲችል መርገም የሆነባቸው አሜሪካውያን የወንዙን መረጋጋት አጥብቀው የሚሹት ተስፋቸው ነው።
በተቃራኒው ደግሞ እያደገ የነበረውን የአሜሪካን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ከወንዙ ውኃ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት በጣም አስፈላጊ የሆነበት ወቅትም ነበር።
እናም አሜሪካውያን ጎርፉን መቆጣጠር፣ ለመስኖ እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ውኃ ማከማቸት ብሎም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማሟላት የሚያስችል ፕሮጀክት ቀርጾ ሥራ መጀመር የወቅቱ መንግሥት አንገብጋቢ ጥያቄ ነው።
ወንዙን የሚያዋስኑ ሰባት ግዛቶች የውኃ አጠቃቀምን መብት ለመመደብ የኮሎራዶ ወንዝ ስምምነት በ1922 ከተፈረመ በኋላ የአሜሪካ ምክር ቤት በ1928 የ"ቦልደር ካንየን ፕሮጀክት ሕግ" አጽድቆ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ ፈቀደ።
ይሁን እንጂ አሜሪካ በታሪኳ ጥቁር ጠባሳ ብላ ካሰፈረቻቸው መጥፎ ታሪኮች ውስጥ አንዱ የሆነው የኢኮኖሚ ድቀት ወቅት ነበርና እንዲህ ያለ ግዙፍ እና ብዙ ገንዘብ የሚጠይቅ ፕሮጀክት መጀመር ቅብጠት ነው የሚሉ ቀላል አልነበሩም።
ስለሆነም ግንባታው የተጀመረው በ1931 አሜሪካ በታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት(Great Economic Depression) ውስጥ በምትገኝበት ወቅት ነበር። በአንጻሩ ደግሞ ፕሮጀክቱ ከመላ ሀገሪቱ ወደ አካባቢው ለሚጎርፉ በሺህ የሚቆጠሩ ሥራ ፈላጊ ሰዎች ከፍተኛ የሥራ ዕድልን እንደሚፈጥር እና አሜሪካውያን ከገቡበት ድባቴ ለማውጣት ይጠቅማል ያሉ መሪዎች ጉዳዩን በችግር ውስጥም ቢሆን ሆነው ሥራውን ለማስጀመር ወደኋላ አላሉም።
"ስድስቱ ኩባንያዎች" በሚል ስያሜ የሚታወቁት የስድስት የግንባታ ድርጅቶች ኮንሶሪየም የግንባታውን ኮንትራት ወስዶ ሥራውን ሠርቷል። ኩባንያው ሠራተኞቹ እና ቤተሰቦቻቸው የሚኖሩበትን "ቦልደር ሲቲ" የተባለ ጊዜያዊ ከተማም መሰረተ።
ሠራተኞች በመጀመሪያ አራት ግዙፍ ዋሻዎችን በመቆፈር ኃይለኛውን የኮሎራዶ ወንዝ አቅጣጫ በማስቀየር ነበር ሥራቸውን የጀመሩት። ወንዙ የሚጓዝበት ቦታ ሸለቋማ በመሆኑ ዋሻ ሰርቶ የውሃን አቅጣጫ ማስቀየር ቀላል ሥራ አይደለም። ብዙዎች ህይወታቸውን ያጡለት እና ትልቅ የኢንጅነሪንግ ጥበብን የሚጠይቅ ነው።
የሙቀቱ መጠን ከ100 ዲግሪ ፋራናይት በላይ በመሆኑ ለአሜሪካውያን ሠራተኞች ይህ በጣም አስቸጋሪና አደገኛ ቢሆንም ለሀገራቸው ትንሣኤ ላባቸውን እና ደማቸውን ሰጥተው የታሰበውን እውን አድርገዋል።
ግንባታው በጣም ፈታኝ የነበረ ቢሆንም ሁቨር ግድብ ከተያዘለት የመጠናቀቂያ ጊዜ አስቀድሞ በ1936 ተጠናቀቀ። በግንባታው ወቅት በአደጋ እና ከሙቀት ጋር በተያያዙ በሽታዎች ሳቢያ ከ100 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ለግንባታው የዋለው የኮንክሪት መጠን ከሳን ፍራንሲስኮ ወደ ኒው ዮርክ ከተማ የሚወስድ ባለ ሁለት መስመር አውራ መንገድም ማሠራት የሚችል ነበር።
በእርግጥ የሁቨር ግድብ የመስኖ ፕሮጀክት ወይም የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ  ብቻ አይደለም። በወቅቱ ከባድ ከነበረው የኢኮኖሚ ድቀት ለመውጣት የብርሃን ቀዳዳ ያገኙበትም ነው። በወቅቱ ለግድቡ ሥራ ያስፈልግ የነበረው የሰው ሃይል ብዙ በመሆኑ ለብዙዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ለግድቡ ሲባል የተገነባው መንገድ እና የተመሰረተው ከተማ ደግሞ ሌላ ያልታሰበ ሲሳይ ይዞላት የመጣው አሜሪካ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደሚባለው ሁቨር ዳም የተኛው ኢኮኖሚዋ እንዲያንሰራራ ምክንያት ሆኖላታል።
ከተጠናቀቀ በኋላ "የቦልደር ግድብ" ተብሎ እንዲሰየም ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ በወቅቱ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩት ሬይ ላይማን ዊልበር "የሁቨር ግድብ" የሚል ስያሜ ሰጥተውታል። ይህም 31ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ኸርበርት ሁቨር በፕሮጀክቱ ልማት ላይ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ መታሰቢያ እንዲሆን ነበር።
ይሁን እንጂ በፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ዲ ሩዝቬልት አስተዳደር ወቅት ስሙ ወደ "ቦልደር ግድብ" እንዲመለስ የተወሰነ ቢሆንም፣ በ1947 ግን በኮንግረስ ውሣኔ ስሙ በቋሚነት ወደ "ሁቨር ግድብ" ተመልሷል።
የሁቨር ግድብ አሁን 94 ዓመት የሞላው ሲሆን፣ በደቡብ ምዕራብ አሜሪካ ለሚገኘው ሚሊየን ሕዝብ የጎርፍ መቆጣጠሪያ፣ እንዲሁም የውኃ እና የኃይል ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ለአሜሪካ የኢንዱስትሪ ልማት ጥንካሬ፣ የሲቪል ኢንጂነሪንግ ልህቀት ማሳያ፣ እንዲሁም ላባቸውን እና ደማቸውን ላፈሰሱ ሠራተኞች ጽኑ የሀገር ፍቅር ማረጋገጫ ማኅተምም ነው።
ለዚህም ነው ዛሬም ድረስ አሜሪካውያን በሁቨር ግድብ እየተጓዙ ሲጎበኙ በአያቶቻቸው ጥበብ እና የሀገር ፍቅር ትጋት እንዲሁም ጥበብ እየተደነቁ የሚመለሱት። ይህ ብቻ አይደለም አሜሪካውያን ሀገራቸው ልዕለ ሃያል እንደሆነች እንዲሰማቸው ካደርጉ ታሪካዊ ክስተቶች ውስጥ አንደኛው ግድብ ሁቨር በመሆኑ በሄዱበት ሁሉ ታላቅነታቸውን ለመመስከር አንገታቸውን ቀና የሚያደርጉት።
በዓለም ላይ ልዕለ ሃያል ሆና ለመቀጠሏ ብዙ ምክንያቶች የምትደረድረው እና በርካታ የዕድገቷ ምስጢሮች የሚተነተኑላት አሜሪካ በታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት እነሱ (Great Economic Depression) የሚሉት ችግር ውስጥ ሆነው የተስፈነጠሩበት ቆራጥ ውሳኔ ይህ ነው። የአሜሪካውያን የኩራት ምንጭ፣ የመስፈንጠሪያ ታሪክ፣ ከድብርት እና ተስፋ መቁረጥ የወጡበት የአያቶቻቸው ቆራጥ የታሪክ እጥፋት የዛሬ ልዕለ ሃያልነት መመስከሪያቸው ሆኗል።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በአጭር ጊዜ ከድህነት ለመላቀቅ ያላቸውን የተጨበጠ ተስፋ የሚያመላክት ሐውልት ነው ሲሉ የባህርዳር ከተማ ነዎሪዎች ገለጹ።
እናቶች ጭምር ከመቀነታቸው ፈትተው የገነቡት ግድቡ ግንባታው ተጠናቅቆ መልሶ የእናቶችን የማገዶ ጭስ ዕንባ ለማበስ መመረቁ ለብዙዎች ተስፋን የፈነጠቀ ነው ብለዋል ነዋሪዎቹ ለኢቲቪ ሲናገሩ።
ሲደረጉብን የነበሩ ፈርጀ ብዙ ጫናዎችን በኅብረት ቆመን፣ በፅናት ተቋቁመን በማለፍ ለምረቃው መድረሳችን የዓድዋ ድልን የሚያስታውሰን ዳግማዊ ዓድዋ ነው ብለዋል።
መላ ኢትዮጵያውያን ያለአንዳች ልዩነት ተረባርበን በራስ አቅም ያለማንም ድጋፍ እውን ያደረግነው ግድቡ ከድህነት ወጥተን አንገታችንን ቀና አድርገን የምንኖርበት ዘመን መቃረቡን አብሳሪ ነው ሲሉ ገልጸውታል።
ላለፉት 14 ዓመታት ያለማቋረጥ ለግድቡ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ ህዝባዊ ተሳትፎው በሌሎች መሰል ፕሮጀክቶች ላይም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል።

በሄናን ግዛት የባህል ቅርስ እና አርኪኦሎጂ ተቋም አርኪኦሎጂስቶች እንደገለፁት፣ ከ8,000 ዓመታት በፊት የነበሩ የቻይና ጥንታዊ የእንጨት የሬሳ ሳጥኖች በጂያሁ ቁፋሮ ቦታ ተገኝተዋል። ይህ ግኝት ቀደምት የሬሳ ሳጥን እና ክፍል ያለው የቀብር ሥርዓት በቅድመ-ታሪክ ቻይና ውስጥ እንደነበረ የሚያሳይ ነው።
በውያንግ አውራጃ በርካታ የአጥንት ዋሽንቶች፣ የዔሊ ዛጎሎች፣ የሸክላ ዕቃዎች እና የድንጋይ መሣሪያዎች የተገኘ ሲሆን ይህም ስለ ቀደምት የቻይና ሥልጣኔ መረጃ ይሰጣል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ዌይ ሺንግታኦ እንደተናገሩት፣ ይህ ግኝት የእንጨት የሬሳ ሳጥኖች ከዚህ በፊት ከታሰበው ከ2,000 ዓመታት ቀደም ብሎ ጥቅም ላይ እንደዋሉ ያመለክታል።
የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች በቁፋሮው ቦታ ከ200 በላይ መቃብሮችን ያገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 10 ያህሉ የእንጨት የሬሳ ሳጥኖች ማስረጃዎች እንዳሏቸው ተገልጿል።
አርኪኦሎጂስቶች እንዳሉት አንዳንድ ሳጥኖች 2 ሜትር ርዝመት፣ 0.6 ሜትር ስፋት እና 6 ሴንቲሜትር ውፍረት አላቸው።
የእነዚህ ግኝቶች መገኘት፣ የቀብር ሥርዓቶች ከበፊቱ ከታሰበው ከ2,000 ዓመታት ቀደም ብሎ መመሥረታቸውን ያመለክታል።

ሬዲዮ ዛሬ ለደረሰበት የዘመናዊ የዕድገት ደረጃ ብዙ ዓመታትን ፈጅቷል፤ የበርካታ ተመራማሪዎችን ጥረትንም ጠይቋል፡፡
እንደነ ቶማስ ኤዲሰን፣ ኒኮላ ቴስላ እና ጎግሊ ኢልሞ ማርኮን የመሳሰሉ የፈጠራ እና የምርምር ጠቢባን ጊዜ እና እውቀታቸውን ለግሰዋል፡፡
እ.አ.አ በ1877 ዓ.ም ኒኮላ ቴስላ መልዕክት እንዴት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ያለ ሽቦ እንደሚተላለፍ በምርምር ደረሰበት፤ ይህንኑ ተከትሎ ሌሎች ተመራማሪዎች በቀደመው ግኝት ላይ በመመርኮዝ ቴክኖሎጂውን ለማሻሻል ሞከሩ፡፡
ማርኮኒ እ.አ.ኤ በ1879 ዓ.ም ከቴስላ የተሻለ እና በገመድ አልባ ቴሌግራፍ አማካኝነት መልዕክትን ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ በሞገድ ኃይል ማስተላለፍ እንደሚቻል በተግባር አረጋገጠ፡፡
ማርኮኒ ራድዮ ሞገድን በመጠቀም መልዕክትን በመሬት፣ በአየር፣ በውኃ እና በሕዋ ላይ 2ኪ.ሜ ብቻ ይጓዝ የነበረውን የሬዲዮ ሞገድ በማሻሻል፣ ከ1 ሺህ እስከ 10 ሺህ ኪ.ሜ መጓዝ እንዲችል የሚያግዝ ቴክኖሎጂ በማስተዋወቁ ዓለም ቆሞ አጨበጨበለት፡፡
የሬዲዮ ታሪክ ሲነሳ ስሙ ጎልቶ የሚነሳው ማርኮኒ በ20 ዓመቱ በሬዲዮ ሞገድ ዙሪያ ምርምር ማድረግ መጀመሩ ይነገርለታል፡፡
ሕልሙ ተሳክቶለት የሬዲዮ ሞገድን በረጅም ርቀት መጓዝ የሚችልበትን የገመድ አልባ የቴሌግራፍ ቴክኖሎጂ አበልፅጎ ለፈጠራ ስራው የባለቤትነት መብት 1889 ያቀረበው ጥያቄ በዓመቱ በ1890 ፀድቆለታል፡፡
የባለቤትነት መብቱን ካረጋገጠ በኋላ በምርምሩ ገፍቶበት በገመድ አልባ የቴሌግራፍ ዘርፍ 800 የሚደርሱ የባለቤትነት መብቶችን ማግኘቱም ይጠቀሳል፡፡
50 ሺህ ፓውንድ በማውጣት በገነባው የሬዲዮ ስርጭት ማስተላለፊያ ጣቢያ አማካኝነት ሬዲዮ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ መልዕክት ማስተላፍ እና መቀበል እንደሚችልም በተግባር በማሳየቱ፣ ግንኙነት መስመራቸው እጅግ ውስን እና ኋላ ቀር የነበሩት መርከቦችም በሬዲዮ መገናኘት በመጀመራቸው እፎይታን አገኙ፡፡
መርከቦች ለአደጋ ሲጋለጡ በሬዲዮ አማካኝነት መልዕክት መለዋወጥ በመቻሉ፣ የአደጋ ጊዜ  ሰራተኞች በፍጥነት ወደ ስፍራው በመምጣት እርዳታ እንዲሰጡ አግዟል፡፡
የታይታኒክ መርከብ ከበረዶ ግግር ጋር ተላትማ ተሰባብራ ስትሰምጥ የ700 ሰዎችን ሕይወት ማትረፍ የተቻለው በቴሌግራፍ በተላለፈ መልዕክት አማካኝነት ነው፡፡
በዚህም ማርኮኒ ላበረከተው አስተዋፅኦ የወርቅ ሜዳሊያ የተሸለመ ሲሆን ለአበርክቶውም አቻ የለውም በማለት ተሞካሽቷል፡፡
የሬዲዮ አባት በመባል የሚጠራው ጎግሊ ኢልሞ ማርኮኒ በ63 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት በተለየበት ወቅት፣ በዓለም ላይ የሚገኙ ሬዲዮ ጣቢያዎች በሙሉ ለ2 ደቂቃ ያሕል ስርጭታቸውን በማቋረጥ ለራዲዮ ፈጣሪው ማርኮኒ ያላቸውን ክብር አሳይተዋል፡፡
የጀርመኑን ዶቼቬሌን በ20 ዓመት፣ የአሜሪካውን የአማርኛ ድምፅ ቪኦኤን በ6 ዓመት የሚበልጠው የኢትዮጵያውያን የበኩር ድምፅ የሆነው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ተደራሽነቱን እያሰፋ ለ90 ዓመታት ዘልቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሬዲዮ አሁን በሀገሪቱ ለሚገኙ በርካታ መገናኛ ብዙኃን አርዓያ መሆን የቻለ ትልቅ የሚዲያ ተቋም ነው ሲል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ገለጸ።
የኢቢሲ አካል የሆነው እና ሥራ ከጀመረ 9 አስርት ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ሬዲዮ 90ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን በማክበር ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋዬ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ አንጋፋው የኢትዮጵያ ሬዲዮ በቅኝ ግዛት ለማቀቁ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ድምፅ መሆን የቻለ ታሪካዊ ተቋም ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ገዢ ትርክቶችን መፍጠር ያስቻሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በድል እንደተወጣ አንስተው፤ በዚህ ሂደት የኢትዮጵያ ሬዲዮ የላቀ አስተዋጽኦ እንደነበረው አክለዋል።
በቀጣይም እንደ ኢትዮጵያ ሬዲዮ ያሉ አንጋፋ ሚዲያዎች እንዲያሳኳቸው የሚጠበቁ ትላልቅ አጀንዳዎች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ዮናታን፤ ልዩነቶቻችንን ወደጎን በመተው አሰባሳቢ የጋራ ትርክቶች ላይ እንድናተኩር ከተቋሙ ብዙ ይጠበቃል ይጠበቃል ብለዋል።
ኢትዮጵያዊነትን በማቀንቀን ላለፉት 90 ዓመታት መንግሥት እና ሕዝብን ሲያገለግል የቆየው አንጋፋው ተቋም በየደረጃው ሀገራቸውን ያገለገሉ በርካታ ባለሙያዎችን ያፈራ መሆኑንም አንስተዋል።

ቻይና በሚቀጥለው ሳምንት የቤጂንግ ዢያንግሻን ፎረም ላይ ከ100 በላይ ሀገራት የመከላከያ ባለስልጣናትን እንደምታስተናግድ አስታወቀች።ይህ የሀገሪቱ ትልቁ የፀጥታ ኮንፈረንስ መሆኑ ተገልጿል።የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ከፍተኛ ኮሎኔል ጂያንግ ቢን እንደተናገሩት "ቬትናም፣ ሲንጋፖር፣ ሩሲያ፣ ፈረንሳይ፣ ናይጄሪያ እና ብራዚልን ጨምሮ ከ100 በላይ ሀገራት ከዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር ለመገኘት ማረጋገጫ ሰጥተዋል" ብለዋል።#EBC #ebcdotstream #China

ቻይና የላቁ የሌዘር መሳሪያዎችን እና አዳዲስ ሚሳኤሎችን አሳይታለች። እነዚህስ አሜሪካን የሚያስፈሩት ለምንድን ነው?
ረቡዕ ዕለት ቻይና የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃትን እና በጃፓን ላይ የተቀዳጀችውን ድል 80ኛዓመት ለማክበር ወታደራዊ ሰልፍ አካሒዳለች።
በቤጂንግ ታላቁ አደባባይ የተደረገው ይህ ዝግጅት፣ ቻይና በቅርብ ጊዜ ከተከሰቱ ወታደራዊ ግጭቶች የተማረችውን ትምህርት በመጠቀም ያፈራቻቸውን የላቁ የጦር መሳሪያዎች አሳይታበታለች።
በሞስኮ የብሔራዊ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት የኮምፕሪሄንሲቭ የአውሮፓ እና ዓለም አቀፍ ጥናቶች ማዕከል ዳይሬክተር ቫሲሊ ካሺን፣ ቻይና በየዓመቱ ወታደራዊ ሰልፍ የማታደርግ በመሆኑ የዚህ ሳምንት ዝግጅት ልዩ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል።
“ይህ ሰልፍ ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ ከነበሩት የቻይና ሰልፎች ፈጽሞ የተለየ ነው። አዲስ ወታደራዊ ጥንካሬ ለማሳየት ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን በቻይና የጦርነት ዶክትሪን ሰነዶች ላይ ለውጦችን ሊያመለክት ይችላል” ብለዋል።
በሰልፉ ላይ የታዩት አዳዲስ ታንኮች፣ የሌዘር መሳሪያዎች እና ሚሳኤሎች ከአሜሪካ ጋር በሚፈጠር ግጭት ውስጥ ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ ስለመሆናቸው ጠቋሚ ናቸው።
ምንም እንኳን ለሰልፉ የሚደረገው ልምምድ ከፍተኛ ትኩረት ቢያገኝም፣ የቻይና ወታደራዊ ኃይል የውጭ ታዛቢዎችን ማስደነቅ ችሏል። DF-61 አህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን (ICBMs) የያዙTransporter erector launchers (TEL) ለመጀመሪያ ጊዜ በወታደራዊ ሰልፉ ላይ ታይተዋል።
ባለ ስምንት-አክስል ቻሲስ ላይ የተገጠመው የዚህ ስርዓት ዝርዝር መረጃ ግን አልተገለጸም። DF-61 ከሩሲያ Yars TEL ጋር በተመሳሳይ ምድብ ውስጥ የሚመደብ ሲሆን፣ ሚሳኤሉን በደቂቃዎች ውስጥ ከየትኛውም የጥበቃ መስመር ላይ ማስወንጨፍ መቻሉ ልዩ ያደርገዋል። DF-61 በአውሮፓውያኑ 2019 ሰልፍ ላይ ከታየው DF-41 TEL የተሻሻለ ሊሆን እንደሚችል ባለሞያዎች ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
DF-41 ከ12,000 እስከ 15,000 ኪሎሜትር የሚደርስ ርቀት የሚሸፍን እና እስከ አስር የሚደርሱ የኒውክለር አረሮችን መሸከም እንደሚችልም ይታመናል።
በተጨማሪም አዲስ የDF-31 ICBM ዓይነት፣ DF-31BJ የተባለው፣ በቤጂንግ ታይቷል። የDF-31A ዓይነት ከ13,000 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት እንዳለው ይታወቃል። እናም ይሄኛው ከቀደሙቱ ሊልቅ እንደሚችል መገመት አያዳግትም::
ሰልፉ የJL-3 አህጉር አቋራጭ ሰርጓጅ-ተወንጫፊ ባሊስቲክ ሚሳኤልንም አሳይቷል። የType 094 “Jin” ክፍል የስትራቴጂክ የኑክሌር ሰርጓጅ መርከቦች እስከ 12 የሚደርሱ እንደነዚህ ያሉ ሚሳኤሎችን መሸከም ይችላሉ።
ብራንደን ጄ. ዌይቸርት በ“The National Interest” መፅሔት ላይ እንደጻፈው፣ ይህ አዲስ ሚሳኤል ቻይና ከአደጋ ነጻ ከሆኑ የባህር ዳርቻ ውሃ ላይ ሆነው አሜሪካን መምታት ያስችላቸዋል።
ዌይቸርት “በአህጉር አቋራጭ ርቀቱ እና በርካታ የኒውክለር አረሮችን የመሸከም አቅሙ፣ JL-3 በኢንዶ-ፓሲፊክ ውስጥ ያለው ወታደራዊ የኃይል ሚዛን ወደ ቻይና እየተሸጋገረ ባለበት ወቅት ቻይና ለአሜሪካ እና ለአጋሮቿ አስፈሪ ተፎካካሪ እንድትሆን ያደርጋታል” ሲሉ ጽፈዋል።
ቤጂንግ የDF-5 ICBM አዲስ ዓይነት የሆነውን DF-5C አሳይታለች። በሰልፉ ላይ እንደተገለጸው፣ ሚሳኤሉ ዓለም አቀፍ ሽፋን አለው። ይህ ማለት ምናልባትም በምህዋር የሚሽከረከር የጦር ራስ የተገጠመለት ሊሆን ይችላል።
የመጀመሪያው ጠጣር ናፍጣ የሚጠቀም DF-5 በአውሮፓውያኑ 1971 አገልግሎት የገባ ሲሆን፣ የተሻሻለው DF-5B ደግሞ የ5,000 ኪሎ ግራም የመሸከም አቅም ያለው ከመሆኑም በላይ የተለመዱ የአየር መከላከያ ስርዓቶችን ማለፍ የሚያስችሉ የላቁ ቴክኖሎጂዎች አሉት።
እንደ ዘገባዎች ከሆነ ሚሳኤሉ በ2017 ተሞክሯል። እስከ 12 የሚደርሱ መርከቦችን በገለልተኛነት ኢላማ ማድረግ የሚችል (MIRV) ስርዓት እንዳለው ይታመናል።
ከሩሲያ Kinzhal ሚሳኤል ጋር የሚመሳሰል አዲስ የJL-1 አየር-ተወንጫፊ ባሊስቲክ ሚሳኤሎችም በቤጂንግ ታይተዋል። በገለጻው መሰረት፣ እነዚህ ከሩሲያ Kinzhal ሚሳኤሎች ጋር የሚመሳሰሉት አውሮፕላኑ ወደተወሰነ ከፍታ እና ፍጥነት ከደረሰ በኋላ ይወነጨፋሉ።
በተጨማሪም፣ CJ-1000 ሃይፐርሶኒክ ረጅም ርቀት የሚጓዝ የክሩዝ ሚሳኤል አስወንጫፊዎች እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ በሕዝብ ነጻነት ሠራዊት የባህር ኃይል አገልግሎት ላይ የሚውሉ YJ-18C ረጅም ርቀት የሚጓዙ የክሩዝ ሚሳኤሎች እና በቻይና አየር ኃይል የሚጠቀሙ CJ-20A ሚሳኤሎችም ለእይታ ቀርበዋል።
አዲስ ታንኮች እና የውጊያ ተሽከርካሪዎች በሰልፉ ልምምድ ወቅት ታዛቢዎች ተመልክተዋል:: ከእነዚህም ውስጥ አዲስ የታጠቁ ተሽከርካሪዎችን ZTZ-201 ታንክን እና ታንክ ደጋፊ የውጊያ ተሽከርካሪዎች ናቸው ለዕይታ የቀረቡት።
በሰልፉ አስተዋዋቂዎች መሰረት፣ ሁለቱም ተሽከርካሪዎች “Type 100” ተብለው ይመደባሉ።
እነዚህ ተሽከርካሪዎች ዘመናዊ ምላሽ ሰጪ ትጥቅ እና ራዳር እንዲሁም ኦፕቲካል ሴንሰሮችን ያካተተ ንቁ መከላከያ ስርዓት የተሻለ ጥበቃ ይሰጣል። ታንኩ ከ120 ሚሜ መድፍ ጋር ሊወዳደር እንደሚችል በሚታመነው ባለ 105 ሚሜ የጦር ግንብ የተገጠመለት ሲሆን፣ በሩቅ የሚሰራ የማሽን ሽጉጥም አለው።
የታንክ ደጋፊ የውጊያ ተሽከርካሪው አውቶማቲክ መድፍ ያለው ሲሆን፣ የስለላ ድሮን የተገጠመለትም ነው። በተሽከርካሪው የኋላ ክፍል የተቀመጡ ሁለት አብራሪዎች ድሮኑን መቆጣጠር ይችላሉ። አሽከርካሪዎቹም በአውግመንትድ ሪያሊቲ መነጽሮች የታጠቁ ናቸው።
የሌዘር ሚሳኤል መከላከያ ስርዓቶች የቻይና መከላከያ ኢንዱስትሪ ለአየር መከላከያ እና ለሚሳኤል መጥለፍ አገልግሎት የሚውሉ በርካታ የሌዘር ስርዓቶችን አዘጋጅቷል። በሰልፉ ላይ LY-1 የባህር ኃይል ሌዘር ስርዓቶች በዊልድ መድረኮች ላይ ታይተዋል።
በተጨማሪም፣ በባለ አራት-አክስል የጭነት መኪና እና በባለ ሶስት-አክስል የታጠቀ ተሽከርካሪ ላይ የተገጠሙ ሁለት ሌሎች የሌዘር ስርዓቶች ታይተዋል። እነዚህ ምናልባትም ለመሬት ኃይሎች የተነደፉ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል።
አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ሀገሮች በአሁኑ ጊዜ በሌዘር ላይ የተመሰረቱ የአየር መከላከያ ስርዓቶችን እያበለጸጉ ነው። እነዚህ ውድ በሆኑ ሚሳኤሎች ስጋቶችን ከመጥለፍ ይልቅ ወጪ ቆጣቢ አማራጭ ይሰጣሉ፣ በተለይ ዋጋቸው ዝቅተኛ የሆኑ የካሚካዜ ድሮኖች ስብስቦችን ለመከላከል የሚያስችሉም ናቸው።
ቻይና ያሳየቻቸው አዳዲስ ሚሳኤሎች እና የሌዘር መሣሪያዎች የአሜሪካን የረጅም ጊዜ ወታደራዊ የበላይነት ለመፈታተን ያላትን የላቀ አቅም ያሳያሉ። የኒውክሌር አቅሟን በዓይነት እና በብዛት እያሰፋች ሲሆን፣ በተለይም አሜሪካን በቀጥታ ሊመቱ የሚችሉ ሚሳኤሎችን አሳይታለች።
እነዚህ ሁሉ ዝግጅቶች ቻይና የአሜሪካን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ለመቀነስ እና በዓለም ላይ ወታደራዊ ኃይሏን ለማስፋፋት እየሰራች መሆኑን ያመላክታሉ።
ወታደራዊ ሰልፉ ደግሞ የቻይና ጦር ከሩሲያ እና ከሌሎች የውጭ አቅራቢዎች በመመካት ይሰራ የነበረበት ጊዜ ማብቃቱንም ያመለክታል።
የቻይና ወታደራዊ ምርምር እና ልማት አሁን በራሱ አቅም የላቁ የጦር መሳሪያዎችን መፍጠር መቻሉን ያሳያል። የሰልፉ ዋና መልእክት ለአሜሪካ እና አጋሮቿ የቻይናን ኃይል በማሳየት፣ በተለይ ታይዋንን በሚመለከት ግጭት ውስጥ ከመግባት በፊት ሁለት ጊዜ እንዲያስቡ ማሳሰብ ነው።
ምንም እንኳን የቻይና ጦር በቴክኖሎጂው እየተሻሻለ ቢመጣም፣ ብዙዎቹ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎቹ በጦር ሜዳ ላይ እስካሁን አልተሞከሩም። በተቃራኒው የአሜሪካ ጦር በኢራቅ እና በዩክሬን ግጭቶች ውስጥ በጦር ሜዳ ላይ የተፈተነ ልምድ አለው። ሆኖም ግን ቻይና አዳዲስ እና የላቁ የጦር መሳሪያዎችን ማምረት እና ማሳየቷ የዓለምን የጦር ኃይል ሚዛን በመቀየር ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተች መሆኑን ያመለክታል።

የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ይፋ ያደረገው “የዓለም አቀፍ የትምህርት ቤት ምግብ ሁኔታ” የተባለ ሪፖርት፣ በትምህርት ቤት የምግብ ፕሮግራሞች ሽፋን ላይ ታይቶ የማያውቅ ዕድገት መመዝገቡን ገልጿል።
ይህ እመርታ ለልማት ዓለም ያልተለመደ መልካም ዜና ሲሆን፣ ከውጭ እርዳታ ጥገኝነት ተላቆ በብሔራዊ መንግሥታት አመራር የሚመራ ፖሊሲ ሆኖ መውጣቱን ያሳያል።
ሪፖርቱ በግልጽ እንደሚያሳየው፣ ይህ ስኬት የተገኘው በየአገራቱ መንግሥታት የፕሮግራሙን የልማት ኃይል በመረዳት እና ብሔራዊ በጀታቸውን በእጥፍ በማሳደግ ነው።
ይህ ቁርጠኝነት፣ ትምህርት ቤት ምግብ ለሕፃናት ደኅንነት ብቻ ሳይሆን፣ ለጤና፣ ለትምህርት፣ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለኢኮኖሚ ዕድገት የሚሰጠውን ሁለገብ ጥቅም ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው።
አዲስ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የትምህርት ቤት የምግብ ፕሮግራሞች የሕፃናትን በትምህርት ቤት መመዝገብ እና ትምህርታቸውን አለማቋረጥ ብቻ ሳይሆን፣ የመማር እና የማሰብ ችሎታቸውንም ከፍ ያደርጋሉ።
ይህ ደግሞ በዛሬው ጊዜ የሚታየውን “የትምህርት ቀውስ” ለመፍታት ውጤታማ መንገድ መሆኑን ያመለክታል። በሪፖርቱ ላይ እንደተጠቀሰው፣ ለእያንዳንዱ 1 ዶላር የሚደረግ ኢንቨስትመንት ከ7 እስከ 35 ዶላር ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያስገኛል።
ፕሮግራሞቹ 466 ሚሊዮን ሕፃናትን ተጠቃሚ ሲያደርጉ ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ7.4 ሚሊዮን የምግብ አብሳይ ስራዎችን ፈጥረዋል።
በተጨማሪም፣ “ከአካባቢው ምርት የተዘጋጀ የትምህርት ቤት ምግብ” (Home-Grown School Feeding) የሚባሉት ሞዴሎች የአካባቢውን የግብርና ምርት በማነቃቃት፣ ለአነስተኛ አርሶ አደሮች የገበያ ዋስትና በመስጠት እና ለአካባቢው ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።
ሪፖርቱ እንደሚያሳየው፣ ፕሮግራሞቹ ለሴቶች እና ለልጃገረዶች ልዩ ጥቅም ይሰጣሉ። ልጃገረዶች በትምህርት እና በጤና ረገድ ከወንዶች የበለጠ ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ ሴቶች ደግሞ በምግብ አቅርቦት ሰንሰለት እና በሌሎች የአካባቢው ስራዎች በመሳተፍ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው እንዲያድግ ይረዳል።
ሪፖርቱ አፍሪካ በዚህ የዕድገት ሂደት ውስጥ ግንባር ቀደም መሆኗን አጉልቶ ያሳያል። በተለይም በኢትዮጵያ፣ በኬንያ፣ በማዳጋስካር እና በሩዋንዳ የተመዘገበው መሻሻል ተስፋ ሰጪ ነው።
ይህ የሚያሳየው የአፍሪካ መንግሥታት የሕፃናትን ደኅንነት እና ትምህርት ከሁሉም በላይ ቅድሚያ መስጠታቸውን ነው።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ በፕሮግራሙ ዕድገት ግንባር ቀደም ከሆኑ አገራት አንዷ ናት። በርካታ ሚሊዮን ህጻናት የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ ናቸው።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደ ጥሩ ተሞክሮ ተጀምሮ ወደ ሌሎች ክልሎች የተስፋፋው የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም፣ በተማሪዎች የመማር ተሳትፎ፣ በትምህርት ቤት መቅረት መቀነስ እና በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ከመቀነስ ባለፈ፣ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እና የአካባቢ ኢኮኖሚን ለማነቃቃት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
ምንም እንኳን ይህ ታላቅ ስኬት ቢመዘገብም፣ ሪፖርቱ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገሮች ላይ ሊደርስ ስለሚችለው አደጋ ያስጠነቅቃል።
እነዚህ ሀገሮች የገንዘብ ምንጭ ውስን በመሆኑ፣ ለትምህርት ቤት ምግብ ፕሮግራሞች የውጭ እርዳታ አሁንም ወሳኝ ነው። ሆኖም፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድጋፍ አቅጣጫ እየተቀየረ እና የሀገር ውስጥ በጀቶች ለብቻቸው ፍላጎቱን ለማሟላት አቅም እያጠሩ መሆኑ የፕሮግራሞቹን ቀጣይነት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል።
ስለዚህ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም የትምህርት ቤት የምግብ ጥምረት አባል የሆኑ ሀገራት፣ በእነዚህ ሀገሮች ላይ ትኩረት አድርገው ድጋፋቸውን መቀጠል አለባቸው።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ሪፖርት፣ የትምህርት ቤት የምግብ ፕሮግራሞች ከቀላል የሰብዓዊ እርዳታነት ወደ ውጤታማ የልማት ፖሊሲ መሸጋገራቸውን አረጋግጧል። ይህ ዕድገት የተገኘው በመንግሥታት ቁርጠኝነት፣ በወሳኝ የገንዘብ ኢንቨስትመንት እና የፕሮግራሙን ሰፊ ጥቅም በማመን ነው።
የኢትዮጵያ እና ሌሎች የአፍሪካ አገራት ያሳዩት አመራር ለሌሎችም አርአያነት ያለው ሲሆን፣ ይህ ስኬት ከቀጠለ በሚቀጥሉት ዓመታት የበርካታ ሚሊዮን ሕፃናትን ሕይወት እና የሀገራትን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመለወጥ የሚቻል ይሆናል።

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በ5 ዓመታት ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ ዓለም አቀፍ የበረራ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር መታቀዱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
የአዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪን ትልቅ እመርታ ላይ የሚያደርስ መሆኑንም ነው አቶ መስፍን የ2018 የኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመትን በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የተናገሩት።
አየር መንገዱ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን በማስፋፋትና አዳዲስ የበረራ መስመሮችን በመክፈት በከፍታ ላይ መሆኑን በመጥቀስ፤ በ2018 በጀት ዓመት የአዲሱ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን ለማስጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ተነሺ አርሶ አደሮችን ወደ አዲስ ቦታ ለማዘዋወር የቤቶች ግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑን በመግለጽ፤ ለአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታም ፋይናንስ እያፈላለግን ነው ብለዋል።
ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያው እጅግ ዘመናዊ ተርሚናል ያለውና ከዓለም ታላላቅ አውሮፕላን ማረፊያዎች ተርታ እንደሚሰለፍ በመጥቀስ፤ አየር መንገዱን ከዓለም ስመ ገናናዎች አንዱ ያደርገዋል ብለዋል።
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሥራ ሲጀምር የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕን ማረፊያም እጅግ ዘምኖ የሀገር ውስጥ በረራን በዓለም አቀፍ የአገልግሎት ደረጃ እንዲሰጥ እንደሚደረግ አስረድተዋል።
አዲሱ ዓመት ለመላው ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ለአየር መንገዱ ደንበኞችና ሠራተኞች የደስታ፣ የፍቅርና የብልፅግና እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
#EBCdotstream #NewYear #EthiopianNewYear #2018EC #EAL #EthiopianAirlines

ይህም እርምጃ በአፍሪካ አህጉር የሚደረገውን የሰዎችና የሸቀጦች እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ ያለመ ነው ተብሏል።
የሀገሪቱ የፀጥታ ሚኒስትር ማሃማዱ ሳና እንደተናገሩት፣ ከእንግዲህ በኋላ ከማንኛውም የአፍሪካ ሀገር ወደ ቡርኪና ፋሶ ለመጓዝ የሚፈልግ ማንኛውም ዜጋ ለቪዛ ክፍያ ምንም አይነት ገንዘብ አይከፍልም።
ሆኖም፣ ቪዛው በነፃ የሚሰጥ ቢሆንም፣ አፍሪካውያን ጎብኚዎች የቪዛ ማመልከቻ ማቅረብ እና ማረጋገጫ ማግኘት እንዳለባቸው ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
ይህ ውሳኔ ቡርኪና ፋሶን ከጋና፣ ሩዋንዳ እና ኬንያ ጋር የአፍሪካን ውህደት ለማስፋፋት የጉዞ ገደቦችን ከተቀላቀሉ ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ አድርጓታል።

የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በዛሬው ዕለት የኒው ዮርክ ስምምነትን የሚደግፍ የውሳኔ ሃሳብ በአብላጫ ድምፅ ማፅደቁን አናዶሉ ዘግቧል።
የኒው ዮርክ ስምምነት ለፍልስጤም እውቅና ለመስጠት እንዲሁም ለእስራኤል-ፍልስጤም ግጭት የሁለት ሀገርነት መፍትሔን ለማስቀጠል ያለመ ነው።
“የፍልስጤምን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ለመመለስ እና የሁለት ሀገርነት መፍትሔን ለመተግበር” በሚል የተዘጋጀው የውሳኔ ሃሳብ በ142 ድጋፍ፣ በ10 ተቃውሞ እና በ12 ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።
የውሳኔ ሃሳቡን ከተቃወሙት መካከል እስራኤል እና አሜሪካ የሚገኙበት ሲሆን፤ በተመድ የእስራኤል አምባሳደር ዳኒ ዳኖን ይህን ስምምነት ተብዬ ማፅደቅ ሰላም ለመፍጠር ቁርጠኝነት አለመኖሩን ያሳያል ብለዋል።
የአሜሪካው ተወካይ ሞርጋን ኦርታጉስ በበኩላቸው፥ ስምምነቱ ግጭቱን ለማስቆም የሚደረጉ ሁነኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን የሚያስተጓጉል ነው ብለዋል።
አክለውም ስምምነቱ ለሀማስ የልብ ልብ የሚሰጥ እና የሰላም ዕድልን የሚጎዳ ነው ብለዋል።
በፈረንሳይ እና በሳውዲ አረቢያ የቀረበውን የኒው ዮርክ ስምምነት ባለፈው ሐምሌ ወር በተመድ ዋና መሥሪያ ቤት ስብሰባ በተካሄደበት ወቅት 17 ሀገራት ፈርመውት እንደነበር ዘገባው አስታውሷል።
#EBCdotstream #UN #GeneralAssembly #Israel #Palestine #NewYorkDeclaration